ሩሲያ እስካሁን ስፑትኒክ ቪ የተባለውን ጨምሮ 3 አይነት ክትባቶችን አስተዋውቃለች
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸው ተነግሯል።
ፑቲን ክትባቱን ይወስዳሉ ከተባለው ጊዜ በአንድ ወር ዘግይተው የወሰዱ ሲሆን፤ ክትባቱን የወሰዱትም በሩሲያ እየተካሄደ ያለውን የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻን ለመደግፍ እንደሆነ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
በአጠቃላይ ከ143 ሚሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ባላት ሩሲያ ውስጥ እስካሁን 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ሁለቱንም ዶዝ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እንደወሰዱም ሪፖርት ያመላክታል።
ሩሲያ እስካሁን ስፑትኒክ ቪ የተባለውን ጨምሮ 3 አይነት ክትባቶችን ያስተዋወቀች ሲሆን፤ ስፑትኒክ ቪ ጥቅም ላይ እንዲውል በሀገሪቱ እውቅና እንደተሰጠው ይታወሳል።
ሁለቱ ክትባች ማለትም ‘ኤፒቫክኮሮና’ እና ‘ኮቪቫክ’ ደግሞ ለድንገተኛ ህክምና ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉም ፍቃድ ተሰጥቷል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ደሜትሪ ፔስኮቭ ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን በሩሲያ ከተመረቱ ሶስቱ ክትባቶች አንዱን እንደሚወስዱ እና የትኛው እንደሆነ በግልጽ አላስታወቁም።