ፕሬዝዳንት ቡሀሪ “ጆ ባይደን በሙስሊሞች ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ መሰረዛቸውን” አደነቁ
ናይጄሪያ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ከሚልኩ ሀገራት አንዷ ናት
“አሜሪካ የዓለም የጤና ድርጅትን እና የፓሪሱን ስምምነትን እንደገና መቀላቀሏ አስደሳች ነው”ብለዋል ፕሬዝዳንት ቡሀሪ
ፕሬዘዳንት ቡሀሪ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ከሙስሊም ሀገራት በሚመጡ ሰዎች ላይ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተጣለው የጉዞ እገዳ መሰረዛቸውን” አደነቁ፡፡
ቡሃሪ ይህንን አስታየት የሰነዘሩት ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ባለፈው ማክሰኞ ዕለት በነበራቸው የቪድዮ ውይይት መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ቡሀሪ “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ናይጄሪያን ጨምሮ በሙስሊም መንግስታት እና በአፍሪካ ሀገራት በብዛት በሚገኙ ዜጎች ላይ የተጣለውን የጉዞ እና የቪዛ ገደብ”ስለሰረዙ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ እግዱን የቀድሞው ፕሬዘዳንት ትራምፕ ነበሩ የጣሉት፡፡
በፈረንጆቹ በ2017 የኤርትራ ፣ የመን ፣ ናይጄሪያ እና ሱዳንን ጨምሮ ከአስር በላይ ሀገራት በሚመጡ ዜጎች ላይ በየትራምፕ አስተዳደር አማካኝነት የጉዞ እገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡ ፖሊሲው በርካታ የፍርድ ቤት ተግዳሮቶች ገጥመውት የነበረ ቢሆንም፤ ተሻሽሎ በዩ.ኤስ.ኤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፈረንጆቹ ሰኔ 2018 ሊፀድቅ ችለዋል፡፡
ጆ ባይደን ወደ መሪነት ከመጡበት ቀን አንስቶ አወዛጋቢ የሆኑት እገዳዎችን ጨምሮ ብዙ የማይወደዱ እና አከራካሪ የሆኑትን የትራምፕ ኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን ቀልብሰዋል፡፡
ናይጄሪያ እጅግ በጣም ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ከሚልኩ ሀገራት አንዷ ናት፡፡
በፈረንጆቹ ከጥቅምት 1 ቀን 2017 እስከ 2018 የበጀት ዓመት ባሉት ጊዝያት ብቻ ከ 7,900 በላይ ለሚሆኑ ናይጀርያውያን የስደተኞች ቪዛ መስጠቱ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቀዋል፡፡
የናይጀርያው ፕሬዝዳንት ቡሀሪ :አሜሪካ የዓለም የጤና ድርጅትን እና የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን እንደገና መቀላቀሏን ማረጋገጧ አስደሳች እንደሆነና በዚህም ለጆ-ባይደን ትልቅ ምስጋና እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት የተቀላቀለችው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ ገና በ30ኛው ቀን ነበር፡፡
ቡሀሪ “በእነዚህ ሁለት መስኮች የአሜሪካ አመራር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወሳኝ ነው”ብለዋል ፡፡
“በእኛ በኩል ናይጄሪያ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ላይ እንደተደነገገው ዓለም አቀፋዊ ጥረቶችን ለመደገፍ በቁርጠኝነት ቆማለች” ሲሉም አክለዋል የናይጀርያው ፕሬዝዳንት ሙሀሙድ ቡሀሪ፡፡
አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራት በፈረንጆቹ በ2015 ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ፤ አሜሪካ ከስምምነቱ የወጣች ብቸኛ ሀገር እንደነበረች የሚታወቅ ነው፡፡