ቻይና መልክ በማየት ብቻ ለሚቀጥሩ ቀጣሪዎች መፍትሔ አለኝ አለች
በቻይና ለስራ ቃለ መጠይቅ የተጠሩ አመልካቾች ተመሳሳይ የፊት ማስክ እንዲያደርጉ ተደርገዋል
አመልካቾቹ ተመሳሳይ የፊት ማስክ ያደረጉት የስራ ቅጥር መድልዎ እንዳይፈጸም በመፍራት ነው ተብሏል
ቻይና መልክ በማየት ብቻ ለሚቀጥሩ ቀጣሪዎች መፍትሔ አለኝ አለች፡፡
በሀገራችን እና በተቀረው ዓለም ቀጣሪ ድርጅቶች መልክ በማየት ስራ ይቀጥሉ ወይም አልያም መልከ መልካም የሆኑ አመልካቾች ቅጥር በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ሲባል ይሰማል፡፡
በቻይናዋ ቼንግዱ ግዛት ያለ አንድ የሎጅስቲክስ ኩባንያ መልከ መልካም አመልካቾች ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ አልያም መልከ ጥፉ አመልካቾች ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይገቡ በሚል ሁሉ አመልካቾች ተመሳሳይ የፊት መሸፈኛ ማስክ እንዲያደርጉ አስገድዷል፡፡
ለስራ ቅጥር የመጡ የስራ አመልካቾች ተመሳሳይ የፊት መሸፈኛ ወይም ማስክ አድርገው ቃለ መጠይቁን ሲያደርጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል፡፡
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ብዙዎች የኩባንያውን ድርጊት አድንቀው ሌሎች ኩባንያዎችም ሊተገብሩ እንደሚገባ ጽፈዋል ሲል ለየት ያሉ የዓለማችንን ክስተቶችን በመዘገብ የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ወደ የተቀረጸው እና ወደ ማህበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቀው ለቃለ መጠይቅ በተጠራ ግልሰብ አማካኝነት ነውም ተብሏል፡፡
ይህን የፊት መሸፈኛ ወይም ማስክ ቃለ መጠይቅ ተደራጊም ሆነ ቃለ መጠይቁን የሚያደርጉ የቀጣሪ ኩባንያ ሰራተኞችም የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
ይህ የፊት መሸፈኛ ወይም ማስክ ቀጣሪዎች የአመልካቾችን ተክለ መልክ በማየት እንዳይቀጥሩ ከማገዙ ባለፈ ለቃ መጠይቅ የተጠሩ አመልካቾች ለጭንቀት እና ሌሎች ተጽዕኖዎች እንዳይዳረጉ ያደርጋልም ተብሏል፡፡