ቀመሩ የሚያመላክተውን የስልክ ቁጥር የደረሱበት እጩ መምህራን ብቻ መመዝገብ ይችላሉ ተብሏል
ቀጣሪ ተቋማት የሚያወጧቸው የስራ ማስታወቂያዎች ሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ከወደ ህንድ ጉጂራት የተሰማው የስራ ማስታወቂያም መነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ ነው የተነገረው።
የሂሳብ መምህርን ለመቅጠር ልዩ ማስታወቂያውን የለጠፈው የባክታሽራም ትምህርት ቤት የመመዝገቢያ የስልክ አድራሻ የለውም።
ይልቁንም አስልታችሁ ድረሱበት ሲል ውስብስብ የሂሳብ ቀመር አስፍሯል።
ማንኛውም አመልካች የተቀመጠውን የሂሳብ ቀመር በመስራት በሚያገኘው ስልክ ቁጥር ድውሎ መመዝገብ ግድ ሆኖበታል።
ታዋቂውን የህንድ የቢዝነስ ሰው ሃርሽ ጎይንካን ጨምሮ በርካቶችም ይህን አስገራሚ የስራ ማስታወቂያ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
ጎይንካ ከትናንት በስቲያ ያጋራው ይሄው የስራ ማስታወቂያ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን፥ ከህንድ አልፎም የመላው አለም ትኩረትን መሳቡን የህንዱ ኤን ዲ ቲቪ ዘግቧል።
በርካታ የሂሳብ ልሂቃንም መልሱ (የትምህርት ቤቱ ስልክ ቁጥር) እንዲህ ነው እያሉ ሲያጋሩ ታይቷል።
ባለአስር ዲጂቱ የሞባይል ስልክ ቁጥር 9428163811 መሆኑን ያለምንም የሂሳብ ማሽን እና ሌላ እገዛ ደርሼበታለሁ ያለ አንድ አስተያየት ሰጪም ቢሊየነሩን ጎይንካ ሽልማት ጠይቋል።
ሌላ አስተያየት ሰጪም “ይህን የሂሳብ ቀመር መመለስ የሚችል ተማሪ ካለ መምህር አያስፈልገውም” ሲል ከባድ ፈተናነቱን ገልጿል።
በርካቶች ግን አስደናቂና እውቀትን የሚፈትሽ ማስታወቂያ ያወጣው የባክታሽራም ትምህርት ቤት ጎበዝ የሂሳብ መምህር ማግኘቱ እንደማይቀር ጽፈዋል።
በምዝገባ ወቅት ቃለመጠይቅን የጨረስ ትምህርት ቤት ተብሎም እየተወደሰ ነው።
ውስብስቡን የሂሳብ ቀመር ፈተው የትምህርት ቤቱን የስልክ አድራሻ በማግኘት ምን ያህል የሂሳብ መምህራን ምዝገባ እንዳካሄዱ እስካሁን አልተገለጸም።