አንቶኒ ብሊንከን የፊታችን እሁድ ቤጂንግ እንደሚገቡ ተገልጿል
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቻይናን ሊጎበኙ ነው።
በታይዋን እና በንግድ ጦርነት ምክንያት ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ቻይና እና አሜሪካ ከፍተኛ መሪዎች ሊገናኙ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የፊታችን እሁድ ወደ ቻይና ይጓዛሉ።
የሚንስትሩ ጉዞ ዋና አላማም ባሳለፍነው ህዳር በሲንጋፖር የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የሁለቱ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ተገናኝተው የመከሩባቸው ጉዳዮች ለውጥ ማምጣታቸውን ለመለካት ነው ተብሏል።
የብሊንከን ጉብኝት በዋሽንግተን እና ቤጂንግ ግንኙነት ታሪክ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ የመጀመሪያው ከፍተኛ መሪ ያደርጋቸዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘት እና የቻይና ኩባንያዎች በዓለም ላይ ያላቸውን የንግድ ስራ ለማወክ የተለያዩ ሰበቦችን በመጥቀስ ማዕቀብ መጣሏ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መበላሸት ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ብሊንከን በቤጂንግ በሚኖራቸው ቆይታም ከአዲሱ የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቼን ዛንግ ጋር እንደሚመክሩ የነጩ ቤተመንግስት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦርነት ጉዳይ የሁለቱ ሃገራት ሚኒስትሮች ዋነኛ መወያያ እንደሚሆንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት በተስማሙባቸው ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቀጠል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።