ሁለቱ ፖለቲከኞች ሰኔ 20 እና ጷግሜ 5 ላይ በአካል ለመከራከር ወስነዋል
ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ የፊት ለፊት ክርክር ለማካሄድ ተስማሙ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በቀጣዩ ዓመት ሕዳር ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታደርግ ይታወቃል፡፡
በዚህ ምርጫ ለይ በስልጣን ለይ የሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁም ሮበርት ኬነዲ ጁኒየር የግል ዕጩ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
ሁለቱ ዋነኛ የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ፓርቲ እጩዎች ምርጫውን እንደሚያሸንፉ የተገመተ ሲሆን እጩዎቹ በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው የእርስ በርስ ጉንተላዎች ምርጫውን የበለጠ አጓጊ አድርጎታል፡፡
የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በስልጣን ላይ ካሉት ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ጋር የፊት ለፊት ክርክር እንዲገጥሟቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡
ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት እና በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኤክስ አካውንታቸው ላይ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ክርክሩን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ሁለቱ ዋነኛ ዕጩዎች ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም አትላንታ በሚገኘው የሲኤንኤን ስቱዲዮ ለመከራከር ተስማምተዋል፡፡
የሁለቱ ፖለቲከኞች የፊት ለፊት ክርክር ለተመልካቾች ዝግ ነው የተባለ ሲሆን ፕሬዝዳንት ባይደን በንግግራቸው መሀል ዶናልድ ትራምፕ ጣልቃ ገብተው እንዳያቋርጧቸው ጥብቅ ህግ አዘጋጅተዋልም ተብሏል፡፡
የአሳማ ኩላሊት ተገጥሞለት የነበረው አሜሪካዊ ህይወቱ አለፈ
ሁለተኛው የፊት ለፊት ክርክር ደግሞ በኤቢሲ ስቱዲዮ ጷግሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን በታሪክ የከፋው ፖለቲከኛ እና ተከራካሪ ነው በሚል አስተያየታቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የክርክሩ ጊዜ በጉጉት እንደሚጠብቁት ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች በተደረጉ ቅድመ ምርጫ ጥናቶች ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡