አሜሪካ ለእስራኤል የአንድ ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያዎች ልትልክ መሆኗን ገለጸች
ሀገሪቱ ከሰሞኑ እስራኤል በንጹሀን ላይ ጥቃት ከፍታለች በሚል የጦር መሳሪያ እንዳይሰጡ ከልክያለሁ ብላ ነበር
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ34 ሺህ በላይ ሆኗል
አሜሪካ ለእስራኤል የአንድ ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያዎች ልትልክ መሆኗን ገለጸች።
ሀማስ ከሳባት ወር በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
ይህን ተከትሎ እስራኤል በሀማስ ስም በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ከፍታለች የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ ሀገራት እና ሰብዓዊ ተቋማት በመሰንዘር ላይ ናቸው።
አሜሪካ ከአንድ ሳምንት በፊት እስራኤል በራፋህ ንጹሀን ላይ ጥቃት አድርሳለች በሚል 3 ሺህ 500 ቦምቦች እንዳይሰጡም አድርጋለች።
ሀገሪቱ ቦምቦቹ እንዳይሰጡ ያገደችው እስራኤል ከአሜሪካ በምታገኛቸው መሳሪያዎች ንጹሀን ተገድለዋል በሚል ምክንያት ነበር።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር የአንድ ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ለእስራኤል ለመስጠት ማቀዳቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ፕሬዝዳንት ባይደን ይህን እቅዳቸውን ካሳወቁ በኋላ ከሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትም ፕሬዝዳንቱ ለእስራኤል በሚሰጡት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ዙሪያ ገደቦችን ስለመጣል እያሰቡ ነውም ተብሏል።
እስራኤል ሀማስ ላደረሰው ጥቃት እየሰጠችው ባለው ራስን መከላከል ዘመቻ ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።
እስራኤል ንጹሀንን በመግደል እና ሌሎች የከፋ ጥቃት አድርሳለች በሚል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት እንድትጠየቅ ግፊቶች እየተደረጉ ይገኛል።
ደቡብ አፍሪካ፣ ቱርክ እና ሌሎችም ሀገራት እስራኤል በጦር ወንጀል እንድትጠየቅ በይፋ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀገራት ናቸው።