የአሜሪካ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንቶች የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ
የአሜሪካ እና የሩሲያ ፕሬዝደንቶች ከባይደን ሹመት በኋላ የመጀመሪያ የስልክ ውይይት አድርገዋል
ሁለቱ መሪዎች የኑክሌር መሳሪያን ለመቀነስ በተደረሰው ሰምምነት ዙሪያ መክረዋል
የሁለቱ ከፍተኛ የኑክሌር መሳሪያ ባለቤት ሀገራት መሪዎች በትናንትናው ዕለት በስልክ ባደረጉት ውይይት በኑክሌር መሳሪያ ቁጥጥር ዙሪያ መምከራቸውን ክሬምሊን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የተደረሰው የኑክሌር ስምምነት ፣ በዓለም ላይ የጦር መሳሪያዎች በተለይ የኑክሌር መሳሪያዎች በከፍተኛ መጠን እንዲቀንሱ ይደነግጋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት የኑክሌር መሳሪያ መጠናቸውን ወደ 1,550 ዝቅ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
በጦር መሳሪያ ቁጥጥር እንዲሁም በጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ሁለቱም ሀገራት ይፋ አድርገዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ሁለቱ ፕሬዝደንቶች በኢራን የኑክሌር ጉዳይ እና በዩክሬን ግጭት ዙሪያም ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች የሚኖሩ ልዩነቶችን በግልጽ አንስተው ለመምከር አሜሪካ ዝግጁ መሆኗ የተገለጸ ሲሆን ፣ ዩክሬንን በተመለከተ አሜሪካ ሉዓላዊነቷን እንደምትደግፍ ባይደን ለሩሲያው አቻቸው አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ መደበኛው መመለስ ለሁለቱም ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንት ፑቲን ሞስኮ እና ዋሺንግተን ግንኙነታቸውን ሰላማዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ስለማቅረባቸው ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
ፕሬዝደንት ባይደን በበኩላቸው ሩሲያ በአሜሪካም ይሁን በአሜሪካ ወዳጆች ላይ ጉዳት ለማድረስ ብትሞክር ፣ አሜሪካ ጠንካራ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ለፑቲን ነግረዋቸዋል ነው የተባለው፡፡
አእምሮው ተመርዞ ከህክምና ወደ ሩሲያ እንደተመለሰ ስለታሰረው አሌክሲ ናቫልኒ እና ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ስለሚባለው ጉዳይም ጆ ባይደን አንስተው መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማስቀጠል በየጊዜው ለመገናኘትም ሁለቱ መሪዎች ተስማምተዋል ነው የተባለው፡፡