ጆ- ባይደን ለሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን “የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያ ጉዳይ” ማንሳታቸው አስታወቁ
ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን፡ “የጋዜጠኛው ሞት ለእኔ እና ለአሜሪካ ትልቅ ጉዳይ ነው” ብለዋል
ለሳዑዲው ልዑል ግድያውን በተመለከተ “እኔ በግሌ የምጠየቅበት አይደለም” ማለታቸው ጆ- ባይደን ተናግረዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ከሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ጋር በነበራቸው ቆይታ የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያ ጉዳይ ማንሳታቸው አስታወቁ።
ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ እንደፈርንጆቹ 2018 በኢስታምቡል በሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ከተገደለ ወዲህ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሳዑዲ አረቢያን ሲጎበኝ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ከጋዜጠኛው ሞት ጋር በተያያዘ በርካታ የአሜሪካ የስለላ ተቋማት የሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ያቀነባበሩት ነው በሚል ልዑሉን ሲከሱ ቆይተዋል።
የአሜሪካ ተቋማት ይህን ይበሉ እንጅ የሳዑዲ የጸጥታ ተቋማት ደግሞ "በቅጥረኛ ገዳዮች " የተፈጸመ ነው የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡
ጆ- ባይደን ወደ ስልጣን በመጡ ማግስትም እንዲሁ የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያን የተመለከተ የደህንነት መረጃ ይፋ ማውጣቱ እና በዚህም የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ተጠያቂ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በተለይም የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት “የሳዑዲ መንግስት ተቺዎቹን የሚገድል እና ተቃዋሚዎቹን የሚያስር ነው” ያሉበት አጋጣሚ አይረሳም።
ለዚህም ነው ሶሞኑ ፕሬዝዳንቱ ሳዑዲ አረቢያን መጎብኘታቸው የሳዑዲ መሪዎችን “ድርጊታችሁ ቀጥሉበት” እንደማለት ነው በሚል ጆ-ባይደን ወደ ሪያድ እንዳያቀኑ በርካታ የተቃውሞ ድምጾች ሲሰሙና ትቸቶች ሲሰነዘሩ ሲደመጡ የነበሩት።
ያም ሆኖ ፕሬዝዳንቱ በመካከለኛው ምስራቅ እያደረጉት ባለው ጉብኝት፤ አሜሪካ አጋር ከሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል ወደ ሪያድ ከመጓዝ ያገዳቸው ነገር የለም።
ትናንት ማምሻው ሪድ የገቡት ፕሬዝዳንቱ ከሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ከሚያነሱዋቸው አንኳር ጉዳዮች እንደፈረንጆቹ 2018 የተገደለው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያ ጉዳይ እንዱ ሊሆን እንደሚችልም በርካቶች ሲያነሱ ቆይቷል፡፡
የጋዜጠኛው ሞት ለእኔ እና ለአሜሪካ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ለልዑሉ ማስረዳታቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ “ እንደ አንድ አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ዝምታን ብመርጥ ከእኔ ስብዕናየ ጋር የሚቃረን ነው፤ እናም ሁሌም ቢሆን ለሰብዓዊነት እንቆማለን" ሲሉም አክለዋል።
ልዑሉ ግድያውን በተመለከተ "እኔ በግሌ የምጠየቅበት አይደለም "ማለታቸውን ያስረዱት ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን፤ እሳቸው " እኔም እንደዛ ነው የሚል ግምት የለኝም "የሚል ምላሽ እንደሰጥዋቸው መናገራቸውም ኤፒ ዘግቧል።