አሜሪካና እስራኤል ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ ለመከላከል የገቡትን ቃል ኪዳን ተፈራረሙ
ጆ-ባይደን፡ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ አሜሪካ “ያላትን ኃይል ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁ ናት” ብለዋል
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ“አሜሪካ እና አጋሮቿ የቀጠናውን ደህንነት እንዳያበላሹ” ሲሉ ባይደንን አስጠንቅቀዋል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን አስታወቁ።
በምዕራብ እየሩሳሌም ሰፋ ያለ ውይይት ያደረጉት ሁለቱ መሪዎች በሰጡት መግለጫ፤ ቃል ኪዳኑን ለመፈራረም የበቁት “I2U2” በሚል በሚታወቀውና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል እና ህንድ ከሚገኙበት ቡዱን ውስጥ ከቀሪዎቹ ሀገራት ማለትም ከህንድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሪዎች ጋር በይነ መረብ ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።
የመሪዎቹ መግለጫ ኢራን ራሷን በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ እንዳትችል አሜሪካ ያላትን “ሁሉንም የብሔራዊ ሃይል አካላት” እንደምትጠቀም ያመላከተ ነበር።
የጋራ መግለጫው አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ ለማስቀጠል ዋሽንግተን የገባችውን ቃልም ያረጋገጠ ነው ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
እንደፈረንጆቹ በ2016 በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ጆ-ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት የ38 ቢሊዮን ዶላር ሪከርድ የሆነ የ10 ዓመት የእርዳታ ፓኬጅ በሁለቱም ሀገራት መካከል መፈረሙ ይታወሳል።
ጆ-ባይደን እና ያዪር ላፒድ ለአሜሪካ እና እስራኤል ግንኙነት ያላቸውን ድጋፍ እና ከኢራን ስለሚገመተው ስጋትም ተናግረዋል።
ላፒድ "የኢራንን ኒውክሌር ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ኢራን የተቀረው ዓለም ኃይል እንደሚጠቀም እንድታውቅ ማድረግ ነው" ብለዋል።
ባይደን በበኩላቸው ኢራንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ ለመከላከል ዲፕሎማሲው የተሻለው መንገድ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነገር ግን ለእስራኤል ደህንነትን "ዋስትና" ነው ያሉትን ነገር አንስተዋል።
ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ አሜሪካ “ያላትን ኃይል ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁ ናት” ሲሉም ነው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተናገሩት።
ጆ-ባይደን እና አስራኤል ይህን ይበሉ እንጂ ፤ ስምምነቱ በቴህራን ሰዎች በኩል የተሰወደደ አይመስልም።
ስምምነቱን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ የአሜሪካው አቻቸው ጆ-ባይደንን አስጠንቅቀዋል።
“አሜሪካ እና አጋሮቿ የቀጠናውን ደህንነት እንዳያበላሹ” ሲሉም ነው ያስጠነቀቁት የኢራኑ ፕሬዝዳንት።
እስራኤል፡ ኢራን እያካሄደች ያለው የኑክሌር ፕሮግራም ዋነኛ የደኅንነቷ ስጋት አድርጋ ብታቀርብም፤ ኢራን ግን የኑክሌር ግንባታዋ ለሰላማዊ አላማ መሆኑን ስትናገር ትሰማለች።