የባይደን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ሚያደረግ ነው ተብሏል
በመካከለኛው ምስራቅ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ከእስራኤል እና ፍልስጤም ቆይታቸው በኋላ አሁን ሪያድ ደርሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ሳዑዲ አረቢያ ሲደርሱ የሳዑዲ ልዑል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደማቅ አቀባበል አድረግውላቸዋል፡፡
“የሰላም ጉዞ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፕሬዝዳንቱ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት፤ አሜሪካ በጊዜ ሂደት እየቀነሰ የመጣው በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ሚያደረግ ነው ተብሎለታል፡፡
የጀ-ባይደን የሳውዲ ጉብኝትም ታዲያ በጣም ተጠባቂና የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ ሊያጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች በጥልቀት የሚመከሩበት እንደሆነ የዓለም አቀፍ ግንኙነትባ ዲፕሎማሲ ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ምሁራኑ “ባይደን ከሳዑዲ አንድ ውለታ ይጠይቃሉ ተብሎም ይጠበቃል፤ ይህም የምታመርተውን ነዳጅ መጠን እንድትጨምር አና ዋጋ እንድትቀንስ ነው” የሚል ሃሳብም ይሰነዝራሉ፡፡
ጆ-ባይደን ለዚህ ጥያቄ ይዘው የሚመለሱት መልስ እና በእያንዳንዱ በርሜል ላይ የሚደራደሯት ሳንቲም ፓርቲያቸው በሚያገኘው በእያንዳንዷ ድምጽ ላይ ጫና ይኖረዋልም ተብሏል።
ባይደን ላይ ከዓረብ አገራት ዘንድ ከሚኖሩ የጥርጣሬ ነጥቦች አንዱ፤ የአሜሪካ መንግስት ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያን የተመለከተ የደኅንነት መረጃ ይፋ ማውጣቱ እና በዚህም የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ተጠያቂ ማድረጉ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ጆ-ባይደን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት “የሳዑዲ መንግስት ተቺዎቹን የሚገድል እና ተቃዋሚዎቹን የሚያስር ነው” ማለታቸው በጉብኝታቸው ወቅት ለሚያነስዋቸው ጥያቄዎች የሳዑዲ መሪዎች ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ ምክንያት ለሆን እንደሚችል ይነሳል፡፡
ሌላው የ“አብረሀም አኮርድ” ተብሎ በሚጠራው ስምምነት እስራኤልን እና የተወሰኑ የዓረብ አገራትን የያዘው ስምምነት በጋራ ጠላትነት የሚያየው ኢራንን ሲሆን፣ ይህ አሜሪካንንም የሚያስማማ ብሎም ባይደን በዚሁ ጉዟቸው አጀንዳ ከሚያደርጉዋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
አስራኤል ከተለያዩ የዓረብ አገራት ጋር ግንኙነት እንድትመሰርት የታለመው የአብራሃም አኮርድ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት ተደርጎ ይነሳል።
“አብረሃም አኮር” በመፈረም ረገድ ባህሬን ከባህረ ሰለጤው ሀገራት ቀዳሚ ስትሆን፤ የተቀሩት ሀገራት ስምምነቱን እንዲፈርሙና ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ ብሎም የቀጠናውም ሰላምና መረጋጋት እውን እንዲያደርጉ የሚለው አሁንም የአሜረካ ጥቅል ፍላጎት መሆኑ ይገለጻል፡፡