በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁመት ላይ የተሳለቀችው ጋዜጠኛ የገንዘብ ቅጣት ተላለፈባት
የሚላን ፍርድ ቤት ጋዜጠኛዋ በሰውነት አካል ማሸማቀቅ ጥፋተኛ ሆና ተገኝታለች ብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሜሎኒ በጋዜጠኛ ላይ ክስ መስርተው ሲያስቀጡ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም
በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ቁመት ላይ የተሳለቀችው ጣሊያናዊት ጋዜጠኛ 5ሺህ ዩሮ ለጠቅላይ ሚንስትሯ እንድትከፍል በፍርድ ቤት ተወስኖባታል፡፡
ጁሊያ ኮርቴዝ የተባለችው ጋዜጠኛ የቀድሞው ፋሽስታዊ መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ እና የጠቅላይ ሚንስትሯን ፎቶ በማያያዝ በኤክስ (ትዊተር) ገጿ ላይ ከለጠፈች በኋላ በሁለቱ ሰዎች መካከል ቅራኔ እንደተፈጠረ ተነግሯል፡፡
ቀጥሎም ጋዜጠኛዋ “ጆርጂያ ሜሎኒ አልፈራሽም፤ 1 ነጥብ 2 ሜትር የምትረዝሚ ሴት በትክክል ራሱ አትታይኝም” የሚል ጽሁፍ በገጿ ላይ አስፍራለች፡፡
ይህን ተከትሎ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጋዜጠኛዋን በሰውነት አካል ማሸማቀቅ ወንጀል ከሰዋታል፡፡
ጉዳዩን የተከታተለው የሚላን ፍርድ ቤት ጋዜጠኛዋ ፈጽማዋለች ባለው ጥፋት የሞራል ካሳ የሚሆን 5 ሺህ ዩሮ ወይም 5456 ዶላር ለጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ እንድትከፍል ወስኖባታል፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሯ ጠበቆች ገንዘቡ ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚለገስ ተናግረዋል፡፡
ሜሎኒ በጋዜጠኛ ላይ ክስ ሲመሰርቱ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም። ባሳለፍነው አመትም ሮቤርቶ ሳቪያኖ የተባለ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጠቅላይ ሚንስትሯ በህገወጥ ስደተኞች ጉዳይ ላይ ባለቸው ጠንካራ አቋም በቴሌቪዝን ሰድቦኛል በሚል በሮም ፍርድ ቤት ከሰውት 1 ሺህ ዩሮ ቅጣትና ለክስ ሂደቱ የወጣውን ወጪ እንዲሸፍን ተፈርዶበታል፡፡
ጣሊያን ጋዜጠኞ በብዛት ከሚከሰሱባቸው ሀገራት መካከል አንደኛዋ ናት። በአለም የሚድያ ነጻነት ደረጃ ማውጫ ላይ በርካታ ጋዜጠኞች ከተከሰሱባቸው 46 ሀገራት ተርታ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
አርኤአይ የተሰኝው በሀገሪቱ መንግስት ባለቤትነት የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣብያ ሰራተኞች ባሳለፍነው ግንቦት ወር መንግስት በስራችን ላይ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው እንደነበር ይታወሳል፡፡