ልዩልዩ
ራሰ በርሃ ደንበኞች የተበራከቱለት የጣሊያን ጸጉርቤት ለምን ተዘጋ?
ጸጉርም ሆነ ጺም የሌላቸው ሰዎች ጸጉርቤቱን ማዘውተራቸው የጣሊያን ፖሊስ ልዩ የምርመራ ቡድን እንዲያዋቅር አድርጎታል
የ55 አመቱ ጸጉር ቆራጭም በወንጀል ተጠርጥሮ ዘብጥያ መውረዱ ተሰምቷል
በጣሊያን ታዋቂ የእግር ኳስ ክለብ መገኛ በሆነችው ዥንዋ የአንዲት አነስተኛ ጸጉርቤት የተለየ አገልግሎት ትኩረትን ስቧል።
የጸጉርቤቷ ደንበኞች ከጭንቅላታቸው ጸጉር የሌላቸው ፊታቸው ላይም ጺም የሚባል ነገር ፈጽሞ የሌላቸው መሆኑ ነው የከተማዋን ዜጎች ብሎም ፖሊስን ጥርጣሬ ውስጥ የከተተው።
የተለያየ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ የጸጉር ቤቷ ደንበኞች ራሰ በርሃ እና ጺም አልባ መሆናቸው ብቻ አይደለም የሚያመሳስላቸው።
በትንሿ ሱቅ ፈልገው የሚሄዱት አገልግሎትም ተመሳሳይ መሆኑና አንዳቸውም ጸጉራቸውንም ሆነ ጺማቸውን ሲስተካከሉ ያለመታየታቸው ጉዳይም የጣሊያን ፖሊስ ልዩ የምርመራ ቡድንን እንዲያዋቅር ማድረጉ ነው የተነገረው።
የፖሊስ የምርመራ ቡድንም በርካታ ራሰ በርሃ ሰዎች የሚያዘወትሯት አነስተኛ ጸጉር ቤት ላይ ምርመራቸውን ሲያደርጉ ጸጉርቤቷ የአደንዛዥ እጽ ማከፋፈያ መሆኗን ያረጋግጣል።
ፖሊስ በፍተሻ ከ100 ግራም በላይ ኮኬይን እና ሌሎች እጾችን እንዲሁም መጠቅለያዎችን ማግኘቱም ተዘግቧል።
የ55 አመቱ የጸጉርቤቷ ባለቤትና ጸጉር ቆራጭም በቁጥጥር ስር ውለው የሚተላለፍባቸውን ቅጣት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።