"የአንድ ህጻን ክብደት እና ቁመት የሀገርን ገጽታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል" -ወጣቱ ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሂዩማን ኑትሪሽን ፕሮፌሰር ናቸው
በ27 ዓመታቸው የሶስተኛ ድግሪ ባለቤት የሆኑት ፕሮፌሰር ቃልአብ አሁን ደግሞ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል
በኢትዮጵያ ካሉ አንጋፋ ዩንቨርሲቲዎች መካከል ዋነኛው የሆነው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለ10 መምህራን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ዩንቨርሲቲው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው መምህራን መካከል ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ አንዱ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ቃልአብ በእድሜ ትንሹ መሆናቸውን ተከትሎ አል ዐይን አማርኛ ቃለ መጠይቅ ለቃለ መጠይቅ ጋብዟቸዋል፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ስለ ልጅነታቸው፣ የትምህርት ቤት ቆይታቸው፣ መምህርነት ሙያቸው እና ስለ ወደፊት እቅዳቸው ቆይታ አድርገዋል፡፡
አል ዐይን፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ እስኪ ስለ ልጅነት ህይወትዎ ይንገሩን
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- የተወለድኩት በአዲስ አበባ ሐምሌ 1977 ነው አሁን 38 ዓመቴ ነው፡፡ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት በየዓመቱ በሚሰጠኝ ካርድ ላይ ሁሌ እምባለው አቅሙን በሚገባ አልተጠቀመም ነበር፣ በልጅነቴ ጎበዝ እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ በትንሽ ጥረት ጥሩ ውጤት አመጣ ስለ ነበር መምህራን አቅሙን አልተጠቀመም እያሉ ካርዴ ላይ ይጽፉ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ቤት ውስጥ አስተዳደጋችሁ ምን ይመስላል? አሁንስ ምን ምን ላይ ናችሁ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- መንታዩን ጨምሮ ሁለት ወንድሞች አሉኝ ሁላችንም ልጆች ወንዶች ነን፡፡ የተለየ አስተዳደግ የለንም አሁን ላይ እኔ ወደ አካዳሚክ አዘነበልኩ፡፡ ወንደሞቼ የቴክኖሎጂ ኢንጅነሪንግ ሙያ ነው ያጠኑት አንዱ አፕል አንዱ አማዞን ኩባንያ ውስጥ ነው የሚሰሩት፡፡ ወላጆቻችን ሳይኖራቸው ነገር ግን ታግለው የምንፈልገውን አድርገውልናል ጥሩ አስተምረውናል፡፡ ቤተሰቦቼ በልጆቻቸው ተሳክቶላቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም ትዳር መስርቻለሁ የሶስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ልጆቼን በጥሩ ስነ ምግባር ከባለቤቴ እና በዙሪያችን ካሉ ቤተሰቦቻችን ጋር ሆነን እያሳደግን ነው፡፡
አል ዐይን፡- የልጅነት ህልምህ ምን ነበር?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ነበር፡፡ ወላጆቼ ልዩ ናቸው፡፡ አባቴም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቋንቋ ፕሮፌሰር ነው፡፡ እናቴ እስከ ሁለተኛ ድግሪ ድረስ ተምራለች፡፡ በወላጆቼ ይህን ነው መሆን ያለብህ ተብዬ አላውቅም፡፡ ኳስ ተጫዋች ነው መሆን እምፈልገው ስል ትችላለህ እያሉ እንድጎብዝ ይደግፉኝ ነበር፡፡ ከዚያ 12ኛ ክፍል ስደርስ በአርጀንቲና አስተናጋጅነት እየተካሄደ የነበረወን ከ16 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ውድድርን በቴሌቪዥን ሳይ እግር ኳስ ለእኔ እንደማይሆን ተረዳሁ እና ወደ ትምህርት ሙሉ ትኩረቴን አደረኩ፡፡ ለራሴ ለአንድ ሀገር 11 ተጫዋች ብቻ ነው የሚያስፈልገው፣ እኔ እግር ኳስ ተጫዋች መሆን እምችለው በ16 ዓመቴ ኢትዮጵያን ወክዬ በዓለም ዋንጫ መሳተፍ ችዬ ቢሆን ነበር ይህን ማድረግ ሳልችል ስቀር ነው የወሰንኩት፡፡
አል ዐይን፡- እና አሁን ወዳሉበት የመምህርነት ሙያ እንዴት ገቡ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- አባቴ ፉል ብራይት ስኮላርሺፕ አግኝቶ ወደ አሜሪካ ሲሄድ እኛም አብረን ሄድን፡፡ በዚያ በአንድ ዓመት ውስጥ ያየኋቸው ብዙ ነገሮች ህይወቴን ቀይረውታል፡፡ በአሜሪካ እያለሁ ብዙ ነገር ተማርኩ፣ እየሰሩ መማር እንደሚቻል፣ ስለ ትምህርት ጥቅም፣ እምወደው ሙያ ምን እንደሆነ እና ሌሎችንም ነገሮች ተምሬበታሁ፡፡ስኮላርሽፑን አጠናቀን ከአሜሪካ ስንመለስ 18 ዓመቴ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ከ30 ዓመቴ በፊት እስከ ፒኤችዲ መማር እንዳለብኝ እና ፒኤችዲን መያዝ አለብኝ ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ከአሜሪካ ስመለስ በኢትዮጵያ ትምህርት ርካሽ መሆኑን ተረዳሁ አሜሪካ ለትምህርት ውድ ነው፡፡ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ድግሪዬን ሰራሁ፡፡
እንደተመረቅሁ ወዲያው የምግብ ሳይንስ ኑትሪሽን ፕሮግራም ሁለተኛ ድግሪ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል ማስታወቂያ ወጥቶ አየሁ እና አባቴም ይህን ነገር እስኪ እየው ሲለኝ ተመዘገብኩ እና ተማርኩ፡ ማስተርሱ እንዳለቀ ዲፓርትመንቱም አዲስ በመሆኑ በዩንቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት የመቀጠር እድል አገኘሁ፡፡ ወዲያው ደግሞ በፈረንሳይ ሀገር ሞምፕሌይ ዩንቨርሲቲ በኑትሪሽን ሄልዝ ሶስተኛ ድግሪ የስኮላርሽፕ እድል መጣ እና ተወዳድሬ በማለፌ ፒኤችዲ ጥናቴን በሶስት ዓመት ጨርሼ ወደ ሀገሬ ተመለስኩ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን 27 ዓመቴ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ነው ወደ መምህርነት ሙያ የገባሁት፡፡
አል ዐይን፡- እስኪ ስለ አባትዎ ንገሩን አባትዎት በዚሁ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው የሚል ነገር ሰምተናል፡፤ እውነት ነው?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- እውነት ነው አባቴ በአዲ አበባ ዩንቨርሲቲ የሊንጉስቲክ ፕሮፌሰር ነው፡፡ በልጅነቴ ጀምሮ አባቴን እየተከተልኩ ወደ ስድስት ኪሎ ዩንቨርሲቲ እመጣ ነበር፡፡ አባቴ እኔን ያሳደገኝ እሚያደርገውን እንዳይ እያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ሁን ብሎኝ አያውቅም፡፡ የመምህርነት ሙያን የወደድኩት በአባቴ ምክንያት ነው፡፡ ተሰጥኦ ያለኝ በማስተማር፣ ማሰልጠን ማጥናት ነው፡፡ ደስ ብሎኝ አየሰራሁ ነው፡፡
አል ዐይን፡- የምግብ ደህንነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ውስጥ የምግብ ደህንነት ፕሮፌሰር መሆን ምን ስሜት ይሰጣል?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- ትልቅ ስሜት ይሰጣል፡፡ ማስተርሴን ስሰራ የጥናት ርዕሴ የምግብ ለስራ ፕሮግራም ነው፡፡ እዚህ ሀገር ላይ የምግብ ችግር ትልቁ ችግር መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ የድሃ ድሃ ተብለው በምግብ ወይም በገንዘብ የሚደገፉ ሰዎች ኑትሪሽንን ነው ያጠናሁት፡፡ ልጆቹ ላይ ያለው ነገር አሁንም አዕምሮዬ ላይ አለ፡፡ የድሃ ድሃ ናቸው፡፡ ከድህነት ለመውጣት ጥሩ አመጋገብ ዋናው ነገር ነው፡፡ የህጻናቱን መቀንጨር ስታይ ሁለት ሶስት ትውልድ በዚሁ ይቀጥላል፡፡ ወላጆችን ከመቀንጨር ላናድናቸው እንችላለን፡፡ የሚቀጥለው ትውልድ የሚድነው ግን የምግብ ደህንነት ከተስተካከለ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በደርግም ጊዜ ሲረዱ ነበር አሁንም እየተረዱ ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት ልንወጣ የምንችለው ህጻናት ላይ ከሰራን ብቻ ነው፡፡ የቀነጨረ ትውልድ ከድህነት ሊወጣ አይችልም፡፡
አንድን ትውልድ ከመቀንጨር ማውጣት የምንችለው ህጻናት ከተረገዙበት ጀምሮ እስከ 2 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በቂ ምግብ ከተመገቡ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ይህን ማድረግ ካልተቻለ የድህነት አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡ 80 በመቶ አዕምሮው ካደገ በኋላ እና ከቀነጨረ በኋላ የሚደረግ ጥረት ብዙም አያዋጣም፡፡ አንድ ዓመት ሁለት ዓመት አመለጠህ ማለት ትውልድ ነው የምታጣው፡፡ ይህን ወቅት ለውጥ ማምጣት ከቻልን ህጻናቱ ቶሎ ይገባቸዋል፡፡ የአካል ችግር አይኖርባቸውም የጉልበት ችግር፣ የዐዕምሮ ብስለት ችግር አይኖርባቸውም፡፡ እኔ ሀገሬን መርዳት እፈልጋለሁ የሚል መለወጥ እፈልጋለሁ የተሻለ ነገር ማበርከት የምችለው እዚህ ላይ ነው ብዬ ስላመንኩ ነው እዚህ ላይ እየሰራሁት ያለሁት፡፡
አል ዐይን፡- የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግር ምን ያህል ነው ማለት እንችላለን በኢትዮጵያ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- የምግብ ዋስትና የብዙ ነገር መሰረት፣ የተለያዩ ተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ ነው፡፡ የልጆች መቀንጨር ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ችግር ነው፡፡ መቀንጨር የምግብ እጥረት ብቻ አይደለም፡፡ የአመጋገብ ባህል፣ አመለካከት እና አመራረት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ጎጃም አካባቢን ብናይ ይህ አካባቢ ለመላው ኢትዮጵያ የሚተርፍ ምግብ የሚያመርት አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ህጻን የመቀንጨር ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ይህ የሆነው ስለ አመጋገብ ያለው አመለካከት አናሳ በመሆኑ ነው፡፡ ምግብን በሆድ መሙላት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በህይወት መኖር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ገበታችን ላይ ያለው የምግብ ስብጥር፣ ስናመርትም የምግብ ስብጥሩን በጠበቀ ሁኔታ መመረቱን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ህጻን ክብደት እና ቁመት የአንድን ሀገር ሁኔታ ይናገራል፡፡ እንደ ሀገር በዚህ መንገድ መለወጥ ከፈለግን ማዕዳችንን በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የጋራ ቅንጅት የግድ ነው፡፡
አል ዐይን፡- የመቀንጨር ችግርን ለመፍታት መፍትሔው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- የኑትሪሽን ፖሊሲ አለን፣ በርካታ ተቋማትም የምግብ ደህንነት ሀገራዊ ችግር መሆኑን አምነው የጋራ ጥረት ለማድረግም ፈቃደኛ መሆናቸውን በፊርማቸው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ግን ቃልን መተግበር ነው፡፡
አል ዐይን፡- እንደ ሀገር ያለብን የምግብ ደህንነት አሁን ላለንባቸው ሀገራዊ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ችግሮች አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆን
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- በሀገራዊ ችግሮቻችን ዙሪያ የስነ ምግብ ሁኔታችን አስተዋጽኦ ዙሪያ ለብቻው የተደረገ ጥናት ባይኖርም ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ ከአመጋገብ ጋር በቀጥታ ይያያዛል፡፡ ሀሳቦች ላይ ተወያይቶ ሀሳብን በሀሳብ መመዝን የሚችል፣ የአዕምሮ እድገት ከአመጋገብ ጥሩ አለመሆን ጋር ግንኙነት እንደሚኖረው መገመት አይከብድም፡፡ በህጻንነት ጊዜያችን የነበረው አመጋገባችን አሁን ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት አቅማችን ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
አል ዐይን፡- በህይወት ዘመንህ ማሳካት የምትፈልገው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- የተወሰነች ግራም የሚመገብ ህጻንን እንዴት መመገብ አቃተን የሚለው ነገር ይቆጨኛል፡፡ ጨረቃ ላይ መውጣት በሚታሰብበት ወቅት እንዴት ይህን ችግር መፍታት አልቻልንም የሚለው ያንገበግባል፡፡ ጉዳዩ ስር የሰደደ እና ችግሩ ከተፈታ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ነው፡፡ እንደ አንድ ተመራማሪ ለዚህ መፍትሔ ማሳየት ነው ህልሜ፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ችግሮች ይመጣሉ፡፡ አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ የሚባል ነገር ምርታማነትን እየቀነሰ ተጨማሪ ችግር ሆኖብናል፡፡ ግን መሰረታዊ ነገር በበቂ ሁኔታ መመገብ ብንችል ዋነኛው ፍላጎቴ ነው፡፡ 2019 እና 2021 ላይ የተደረጉ የስነ ምግብ ጥናት መሰረት እንደ ሀገር ዝቅተኛውን አመጋገብ የሚያሟሉ ህጻናት ቁጥር እጅግ ትንሽ ነው፡፡ ይህ እዉነታ ተቀይሮ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ጥሩ አመጋገብ ያላቸው ህጻናት መጠን 14 በመቶው ብቻ ነው፡፡ በከተማ ያለውን ብናይ እንኳን 20.4 በመቶ ነው፡፡ ይህ ሲቀየር ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ችግሩ ድህነት ብቻ አይደለም የተሻለ ኢኮኖሚ ያላቸው ቤተሰቦችም ስብጥሩን የጠበቀ ምግብ ለልጆቻቸው እየመገቡ አይደለም፡፡ ይህ ተቀይሮ 90 እና 100 ፐርሰንት እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ የነገ ትውልድ ተነጋግሮ መግባባት እንዲችል፣ ብሩህ አዕምሮ ኖሮት ሀገርን መለወጥ እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ጥሩ ተመግቦ ያላደገ ህጻን ሲያድግ ለተለያዩ ህመሞች የተጋለጠ ይሆናል፡፡ አሁንላይ የምናያቸው ችግሮች ሁሉ እየተጠራቀሙ ይመጣሉ፡፡ ይህንን ለመፍታት አመጋገባችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
አል ዐይን፡- እርስዎ ወጣቱ ፕሮፌሰር ተብለዋል በወጣትነት ይህን መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- ያው ከእድሜ ጋር ድካም አለ፤ አንድን ነገር በጊዜ ስትደርስበት የበለጠ እና ብዙ የመስራት እድል ታገኛለህ፡፡ በዚች እድሜ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ 15 ፒኤችዲ እና ከ50 በላይ ሁለተኛ ድግሪ ሰልጣኞችን አስተምሬያለሁ፡፡ እድሜውን ከሰጠኝ ደግሞ በቀጣዮቹ ዓመታት ከዚህ የበለጡ ሰዎች ቁጥር በማሰልጠን እውቀት እየተባዛ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ በጊዜ እና በወጣትነት ፕሮፌሰር መሆን ለሀገር ብዙ አበርክተህ ታልፋለህ፡፡ እኔ ስራዬ እና ኑሮዬ አንድ ነው ይህንን ለማድረግ ብዬ በተለየ መንገድ ያደረኩት ነገር የለም፡፡ ስራዬን ከልቤ ነው የምወደው፡፡ ቤቴም ቢሮም ስራ ላይ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ የሪሰርቸር የዘወትር ስራ ነው፡፡
አል ዐይን፡- ፕሮፌሰር ለመሆን መስፈርቱ ምንድን ነው?
እንደ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ህግ መሰረት ፕሮፌሰር ለመሆን መስፈርቱ መጀመሪያ ፒኤችዲ ያስፈልጋል፣ ከዚያ በኋላ ተባባሪ ፕሮፌሰር ለመሆን አራት ዓመት ማስተማር፣ ሳይንቲፊክ ጆርናል ላይ ጥናቶችን ማሳተም፣ከዚያ ተባባሪ ፕሮፌሰር ይኮናል፡፡ ከዚያ አራት ዓመት ማስተማር፣ ጥናቶችን ማሳተም፣ አስተዳድራዊ አስተዋጽኦዎችን ማበርከት ከዚያ በሃገር እና አለም አቀፍ ገምጋሚዎች ስራዎቹ ተገምግመዉ መስፈርቱ እንደተሟላ ሲታመንበት ወደ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ይሸጋገራል፡፡ ዋና ዋና መስፈርቶቹ እነዚህ ናቸው፡፡
አል ዐይን፡- እስካሁን በነበሮት የሪሰርቸርነት ጊዜ ምን አበረከቱ?
በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች እና ተቋማት ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ማስተርስ እና ሶስተኛ ድግሪ ሰልጣኞችን ማስመረቄ ለሀገር ብዙ ጥቅም አለው ብዬ አስባለሁ፤ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ በዓለም የስነ ምግብ ፖሊሲ ኮሚቴ በአባልነት እያገለገልኩ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የሚመራበትን የልጆች አመጋገብ እና ስነ ምግብ ፖሊሲን ካዘጋጁት መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ከ140 በላይ ጥናቶችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትሜያለሁ፡፡ እስካሁን እነዚህን ለሀገሬ ፣ ለዩንቨርሲቲዬ እና ለዓለም አበርክቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ወደ ፊት ብዙ እንደማበረክት ይሰማኛል፡፡
አል ዐይን፡- ስንት ቋንቋዎችን ይችላሉ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡-አማርኛ፣ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን እችላለሁ፡፡ ቋንቋ በቻልክ ቁጥር ጥቅምህ በዛው ልክ ይሰፋል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት እንግሊዘኛ አይችሉም ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ወደነዚህ እና ሌሎች ሀገራት እየተጓዝኩ ብዙ ስራዎችን እሰራለሁ ቋንቋዎቹን በመቻሌ ብዙ እድሎችን አግኝቻለሁ፡፡ ወጣቶች በተቻለ መጠን ብዙ ቋንቋዎችን እንዲማሩ እመክራለሁ፡፡
አል ዐይን፡- ወጣቶች የመምህር ሙያን አሁን ላይ ከሚገኘው ጥቅማ ጥቅም ጋር በማያያዝ ሙያውን ሲርቁ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- ወጣቶችን የምመክረው ከማንነታቸው ጋር የሚስማማ ሙያን እንዲሰሩ ነው፡፡ መሆን የሚፈልጉትን ሙያ ነው መማር ያለባቸው፡፡ ሙያውን ከልብ መውደድ ካለ ገንዘቡ ዋነኛ ዓላማ ሊሆን አይችልም፡፡ የአካዳሚክ እርከኑ ሊገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን በዘርፉ እከሌ የሚባለው ሰው ያጠናው ጥናት ተብሎ የሚጠቀስ ስራ መስራት አይቻልም፡፡ ብዙ ሰው ይህ ሙያ ያበላል ብሎ ይገባል፡፡ ያለነው በድሃ ሀገር ውስጥ ነው፡፡ የመምህር ደመወዝ ትንሽ ነው፡፡ ግን ሙያውን ወደኸው ከገባህ በተለይም በዩንቨርሲቲ ውስጥ የሚሰሩ መምህራን ጥሩ እውቀት ካለ የገንዘብ ጉዳይ ትልቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ዩንቨርሲቲ ማለት ዓለም ነው በሀገር ብቻ አይታጠርም፡፡ ስራህን ያየ ሰው እውቀትህን ለመግዛት ይመጣል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ የመመህር ደመወዝ ወርሃዊ ክፍያው ብቻ አይደለም፡፡ የሰራሃቸው ጥናቶች፣ ጥናቶችህን ያየ ሰው አስተያየት ሲሰጥህ፣ ያሰለጠንካቸው ተማሪዎችህ ሲሳካለቸው ስታይ በገንዘብ የማይተመን ደስታን ይሰጣሉ፡፡ ግን ሙያውን ወደኸው ከገባህ ፈተናን ትቋቋማለህ፣ የምትሰራቸው ጥናቶችም በተለያዩ ተቋማት ይወደዳሉ፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የገንዘብ ጉዳይ ዋነኛ ትኩረትህ አይሆኑም ያኔ ጥቅሞች እየሰፉ ይመጣሉ አብረሃቸው የምትሰራቸው ተቋማት ይበዛሉ፡፡
አል ዐይን፡- በእኛ በኩል ያለን ጥያቄ የእስካሁኑ ነበር፡፡ ለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን!!
ፕሮፌሰር ቃልአብ ባዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡