አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጠው
የኦሎምፒክ እና የአለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ የሀገሩ ሰንደቅ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋም የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ ያውለበለበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የክብር ዶክትሬት ተሰጠው።
ለአትሌት ቀነኒሳ የክብር ዶክትሬቱን ያበረከተው የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ነው።
በበቆጂ ተወልዶ በአለም የሩጫ መድረክ የነገሰው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከፈረንጆቹ 2003 የአለም ሻምፒዮን አንስቶ ጉዳት እስከፈተነው ድረስ ድልን በድል ላይ እየደረበ ዘልቋል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሶስት የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ሻምፒዮን ነው። በዓለም ሻምፒዮናም አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል።
ከሀገሩ ልጅ ምሩጽ ይፍጠር “ማርሽ ቀያሪነትን” የተማረው ቀነኒሳ ፥ በዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮም 11 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን አለምን አስደምሟል።
በቻይና መዲና ቤጂንግ በተደረገው የ2008ቱ ኦሎምፒክ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ሻምፒዮን የሆነበት ውድድር በበርካታ ኢትዮጵያውያን አይረሴ ነው።
ቀነኒሳ በ2004ቱ የአቴንስ ኦሎምፒክም በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ፤ በ5 ሺህ ሜትርድ ደግሞ የብር ሜዳልያ ማግኘቱ አይዘነጋም።
በቤልጂየም እና ሆላንድ ሪከርድን የሰባበረው የሀገር ባለውለታ ቀነኒሳ በቀለ ከ2009 ጀምሮ ወደ ማራቶን ያዘነበለው ሲሆን፥ በፈረንሳይ እና ጀርመን በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች አሸንፏል።
በበርሊን ማራቶን በ2019 በ2 ስአት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በማጠናቀቅ ያሸነፈበት ውጤትም ለሪከርድ የቀረበ ነበር።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የኦሎምፒክ የማራቶን ሪከርድ የመስበር ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ ተደምጧል።
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ አትሌት ኢትዮጵያን ከፍ አድርገሃል ብሎ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋም የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል።
ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ለሰላማዊ የመፍትሄ አማራጮች እና እርቅ ለሰጡት ትኩረትና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸው።