ሀማስ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ውድቅ አደረገ
በካይሮ በተካሄደው ድርድር ከግብጽ እና ኳታር አደራዳሪዎች በጨማሪ የአሜሪካ የስለላ ድርድት ሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ተገኝተዋል
የሀማስ ታጣቂ ቡድን በአደራዳሪዎቹ ግብጽ እና ኳታር በኩል የቀረበው የእስራኤል የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ የየትኛውምን የፍልስጤም ታጣቂ ፍላጎት አያሟላም ብሏል
ሀማስ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ውድቅ አደረገ።
የሀማስ ታጣቂ ቡድን በዛሬው እለት እንዳስታወቀው በአደራዳሪዎቹ ግብጽ እና ኳታር በኩል የቀረበው የእስራኤል የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ የየትኛውምን የፍልስጤም ታጣቂ ፍላጎት አያሟላም።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ ለመቀበል አስቸጋሪ ነው ያለውን ምክረ ሀሳብ አጥንቶ ለአደራዳሪዎቹ መልስ እንደሚሰጥ ገልጿል።
አንድ የሀማስ ባለስልጣን በካይሮው ንግግር ላይ እስራኤል ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳብ ውድቅ ማድረጉን በትናንትናው እለት ለሮይተርስ ተናግራል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ስደተኞች የመጨረሻ መሸሸጊያ የሆነችውን ለማጥቃት ቀን መቆረጡን ተናግረዋል።
እስራኤል እና ሀማስ ባለፈው እሁድ ወደ ግብጽ የተደራዳሪ ቡድን ልከው ነበር። በካይሮ በተካሄደው ድርድር ከግብጽ እና ኳታር አደራዳሪዎች በተጨማሪ የአሜሪካ የስለላ ድርድት ሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ተገኝተዋል።
በዚህ ድርድር ላይ የበርንስ መገኘት አሜሪካ ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ እና እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማድረግ ጫና እየጨመረች መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
ነገርግን ወረራ የፈጸመችው እስራኤል የአቋም ለውጥ አለማሳየቷን እና ምንም አዲስ ነገር አለመኖሩን የገለጸው ሀማስ ድርድሩ መሻሻል አላሳየም ብሏል።
ሀማስ እስራኤል ወረራዋን እንድታቆም፣ ጋዛን ለቃ እንድትወጣ እና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል።
እስራኤል በአንጻሩ የጋዛን የደህንነት ቁጥጥር በስሯ ሆኖ እንዲቀጥል ትፈልጋለች።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ ድንበር ጥሶ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ስድስት ወር አልፎታል።
የጋዛ የጤና ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በእስራኤል ጥቃት እስካሁን ከ32ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።