ኬንያ ፋይዘር የተሰኘውን ክትባት መሰጠት አዘገየች
ሀገሪቱ ክትባቱን ያዘገየችው ክትባቱን መስጠት የሚያስችል መርፌ ባለመኖሩ ነው
ኬንያ ፋይዘር የተሰኘውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት መስጠት ማዘግየቷን አስታወቀች
የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አሜሪካ ሰራሽ የሆነው ፋይዘር የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለዜጎቿ መስጠት ትፈልጋለች።
ይሁንና ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ሲሪንጅ ወይም መርፌ ባለመኖሩ ክትባቱን ለማዘግየት መገደዳቸውን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተናግሯል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በኬንያ በስራ ላይ የነበሩት የክትባት መርፌዎች 0 ነጥብ 5 ሚሊ ሊትር መጠን መከተብ የሚያስችሉ ሲሆን የፋይዘር ክትባት ግን ለአንድ ሰው 0 ነጥብ 3 ሚሊ ሊትር መጠን ነው።
በዚህም ምክንያት ፋይዘር ክትባትን መስጠት የሚያስችል መርፌ እስኪዘጋጅ ድረስ እንደማይሰጥ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በኬንያ ከ249 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን አንዳጡ የጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ መረጃ ያስረዳል።
በዓለማችን ደግሞ 219 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በኮቪድ ሲጠቁ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
አሜሪካ ህንድ እና ብራዚል በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ደቡብ አፍሪካ፤ሞሮኮ እና ቱኒዝያ ደግሞ ከአፍሪካ በርካታ ዜጎቻቸውን በሞት ያጡ ሀገራት እንደሆኑም የዚሁ ተቋም ሪፖርት ያስረዳል።