የ1998ቱ የአሜሪካ ኤምባሲ የሽብር ጥቃት ተጎጂ ኬንያውያን ካሳ ጠየቁ
ተጎጂዎቹ በጥቃቱ ሰለባ የሆንነው በጸጥታ አካሉ ቸልተኝነት ነው ብለዋል ባቀረቡት የክስ ዝርዝር
ተጎጂዎቹ ከጥቃቱ በፊት የነበሩ ሁኔታዎችን የሚያጣራ መርማሪ ኮሚሽን እንዲቋቋምም ጠይቀዋል
እ.ኤ.አ የ1998ቱ በኬንያ ናይሮቢ የአሜሪካ ኤምባሲ የሽብር ጥቃት ተጎጂ ኬንያውያን የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያ መንግስት እንዲክሳቸው ጠየቁ፡፡
ተጎጂዎቹ በጥቃቱ ሰለባ የሆንነው በጸጥታ አካሉ ቸልተኝነት ነው ሲሉ ፊርማቸውን አሰባበስበው ክስ መስርተዋል፡፡
ከጥቃቱ በፊት የነበሩ ሁኔታዎችን የሚያጣራ መርማሪ ኮሚሽን እንዲቋቋምም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጠይቀዋል፡፡
የጸጥታ አካሉ ጥቃት ሊፈጸም እንደሆነ ቀድሞ ያውቅ ነበር ያሉት ተጎጂዎቹ ጥቃቱን ሊያስቆም የሚችል አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ባለመውሰዱ መንግስት በህግ እንዲጠየቅ እንፈልጋለን ስለማለታቸውን ዘ ኔሽን ዘግቧል፡፡
በአል ቃይዳ ተፈጽሟል በተባለለት የኤምባሲው ጥቃት 280 ኬንያውያንን ጨምሮ 12 አሜሪካውያን መሞታቸው ይታወሳል፡፡
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ሱዳን የሽብር ቡድኑን መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን ጨምሮ አባላቱን ትደግፍ ነበር በሚል በአሜሪካ የሽብርተኞች ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍራ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ሆኖም የተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ካርቱምን ከጥቁር መዝገብ ዝርዝሩ ሰርዟታል፡፡
ምክንያ ደግሞ ታንዛኒያን ጨምሮ በተፈጸመው በዚህ የሽብር ጥቃት ከተጎዱ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፍታት መስማማቷን እና ወደ ተጎጂዎች አካውንት 335 ሚሊዮን ዶላር ማስተላለፏን ተከትሎ ነው፡፡