የኮሮና ክትባት አያስፈልግም ይሉ የነበሩ አንድ ኬንያዊ ሐኪም በቫይረሱ ህይወታቸው አለፈ
ሐኪሙ ክትባቱን የተቃወሙት ኮሮና ቫይረስን በሙቀት እና በጸረ ወባ መድሃኒት መከላከል ይሻላል የሚል አቋም ነበራቸው
ሐኪሙ ከአምሰት ዓመት በፊት የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል ለልጃገረዶች የሚሰጠውን ክትባት ተቃውመው ነበር
ዶክተር ስቴፈን ካራንጃ የተባሉት ኬንያዊ ሐኪም አስተራዘኒካ የተሰኘውን እና በመላው ኬንያ በመሰጠት ላይ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተቃውመው ነበር።
ሐኪሙ ከትባቱን የተቃወሙት ኮሮና ቫይረስን በሙቀት፤በምግብ እና ለጸረ ወባ ህክምና በሚሰጡ እንክብሎች መከላከል ይቻላል የሚል አመለካከት ስለነበራቸው እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህንን ዶክተር ስቴፈን በመጨረሻም በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ህይወታቸው ማለፉ ተገልጽል።
ዶክተር ስቴፈን የካቶሊክ ሐኪሞች ማህበር ሊቀመንበር ሲሆኑ ቤተክርስቲያኗ በዚህ አቋማቸው ምክንያት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።
ይሁንና የዶክተር ስቴፈንን ሀሳብ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተጨማሪ የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጅት ውድቅ አድርጎታል።
ኬንያ ከ1ሚሊዮን በላይ የአስተራ ዜኒካ ክትባትን ከዓለም ጤና ደርጅት የተረከበች ሲሆን ክትባቱን ለዜጎቿ በመስጠት ላይ ትገኛለች።
እስከ ዛሬ ድረስ በኬንያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 160 ሺህ የደረሰ ሲሆን ከ2ሺህ 700 በላይ ዜጎቿን ደግሞ በሞት ተነጥቃለች።
የማህጸን ሐኪም የሆኑት ዶክተር ስቴፈን በፈረንጆቹ በ2014 በኬንያ ለልጃገረዶች ይሰጥ የነበረውን የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ተቃውመው ነበር።
ዶክተር ስቴፈን ክትባቱን የተቃወሙት የማህጸን በር ክትባቱ የልጃገረዶቹን ቀጣይ ሀይወት ይጎዳል በሚል ምክንያት ነበር።