ዚምባብዌ የዓለማችን የዝሆን ሀብታም አገር ናት
ኬንያ ባላት የዝሆኖች ብዛት የዓለማችን 4ኛዋ አገር ተባለች።
ከዓመታት በፊት በኬንያ የዝሆኖች ቁጥር በህገወጥ አዳኞች ምክንያት ተመናምኖ በመጥፋት ላይ ያለ የዱር እንስሳ ነበር።
አገሪቱ በሰራችው የዝሆኖች ጥበቃ ምከንያት እንስሳቱን ከመጥፋት ታድጋ ቁጥሩን ወደ 36 ሺህ 280 ከፍ ለማድረግ መቻሏን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በዚህም ምክንያት ኬንያ ከዓለማችን በዝሆኖች ቁጥር አራተኛዋ አገር መሆኗ ተገልጿል።
በዓለማችን ዚምባብዌ፣ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ ባሏቸው የዝሆኖች ቁጥር ከ1ኛ አስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ የያዙ አገራት እንደሆኑ ዘገባው አክሏል።
የኬንያ የዱር እንስሳት ዳሰሳ ጥናት እንደሚያስረዳው ኬንያ ከዝሆኖቿ በተጨማሪ ቁጥሩ በመናመን ላይ የነበረው አውራሪስ በተሰራው የጥበቃ ስራ ወደ 1 ሺህ 739 ከፍ ብሏል።
የኬንያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የአገሪቱ የዱር እንስሳት አገልግሎት ተቋም የሰራው የእንስሳት ጥበቃ ስራን የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በተለይም ህገወጥ የዱር እንስሳት ማዘዋወርን እና ማደንን ለማስቀረት ጥሩ ስራ ሰርተዋል ያሉት ፕሬዘዳንት ኬንያታ በቀጣይ በሶስት ዓመት አንዴ የዱር እንስሳት ቆጠራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።