ኬንያ ወንጀልን ለመከላከል በሚል ከ 5,000 በላይ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን አቃጠለች
ሕገ-ወጥ መሳሪያዎችን ማቃጠሉ በ2020 በአፍሪካ የመሳሪያ ድምጾችን ጸጥ ማሰኘት ከሚለው ጥሪ ጋር ተዛማጅ መሆኑን ፕሬዝደንት ኬንያታ ገልጸዋል
ኬንያ ከዚህ ቀደምም ከ8 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያዎችን ማቃጠሏን አስታውቃለች
ኬንያ ትናንት ረቡዕ ዕለት 5,144 ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እንዲሁም ጊዜ ያለፈባቸው በመንግስት የተያዙ ቀላል መሳሪያዎችን አቃጥላለች፡፡ መሳሪያዎቹን ማቃጠሉ ወንጀልን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
መሳሪያዎቹን ለማቃጠል እሳት የለኮሱት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው፡፡
ፕሬዝደንት ኬንያታ ሕገ-ወጥ እና ጊዜ ያለፈባቸው መሳሪያዎችን የማቃጠሉ ተግባር በ2020 በአፍሪካ የመሳሪያ ድምጾችን ፀጥ ማሰኘት ከሚለው የአፍሪካ ሕብረት ጥሪ ጋር ተዛማጅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ አክለውም ፣ ምንም እንኳን የአፍሪካ ሕብረት ዕቅድ በተጠናቀቀው ዓመት ሙሉ በሙሉ ባይሳካም ፣ ኬንያን ጨምሮ አንዳንድ ሀገሮች ወደዚያ ግብ ለመድረስ ጥሩ እድገት አሳይተዋል ብለዋል።
በናይሮቢ ዳርቻ በምትገኘው በካጂዶ አካባቢ መሳሪያዎቹን ባቃጠሉበት ወቅት “ህገ-ወጥ መሳሪያዎችን በይፋ በማስወገድ ፣ በአነስተኛ ና ቀላል የጦር መሳሪያዎች የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ ቁርጠኛ እና ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ አሳይተናል” ብለዋል ፡፡
መንግስታቸው የሁሉም ኬንያውያንን ሕይወት የማስጠበቅ ህገ-መንግስታዊ ስልጣን እንዳለው በመግለፅ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን የመቆጣጠሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዝደንት ኬንያታ ገልፀዋል ፡፡
የኬንያው መሪ ሁሉንም ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ በጎሳዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚያቀጣጥሉ መሪዎችን መንግስታቸው እንደማይታገስ አስጠንቅቀዋል፡፡
ኬንያ ከዚህ ቀደምም በፈረንጆቹ በ2019 ከ 8 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያዎችን ማቃጠሏን አስታውቃለች፡፡
አፍሪካ ለአነስተኛ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች መስፋፋት የተጋለጠች ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው የአህጉሪቱ ክፍሎች በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁከቶች የበርካቶችን ሞት አስከትሏል፡፡