ኢትዮጵያውያኑ ይጓዙበት የነበረው ተሸከርካሪ መጋጨቱን ተከትሎ መያዛቸውን የኪሪያንጋ ፖሊስ አስታውቋል
ኬንያ በህገወጥነት ጠርጥሬያቸዋለሁ ያለቻቸውን 14 ኢትዮጵያውያን ማሰሯን አስታወቀች፡፡
ኢትዮጵያውያኑ የታሰሩት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሲሆን ኪሪያንጋ ግዛትን በማቋረጥ ላይ ነበሩ ተብሏል፡፡
ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ ኪቢርጊዊ በተባለ የግዛቲቱ መንደር መጋጨቱን ተከትሎም ነው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የገቡ አለበለዚያም አቋርጠው ሲያልፉ የነበሩ ሳይሆኑ አልቀረምም ነው ፖሊስ ያለው፡፡
ከ14ቱ መካከል 10ሩ በ12 እና 13 የእድሜ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ህጻናት እንደሆኑም አስታውቋል፡፡
የምዕራብ ኪሪያንጋ ፖሊስ አዛዥ ማርታ ኒጌች “ተሽከርካሪውን ስንፈትሽ አብዛኞቹ ህጻናት ሆነው አግኝተናቸዋል” ሲሉ ለተለያዩ የሃገሪቱ ሚዲያዎች ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ወደ ሚገኝና ባሪቾ ወደተባለ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ኢትዮጵያኑ በአደጋው የደረሰባቸው ጉዳት እንደሌለም ነው ፖሊስ አዛዧ የተናገሩት፡፡
ኒጌች ኢትዮጵያውያኑ ያለ ምንም ህጋዊ ፈቃድ ወደ ኬንያ በመግባታቸው ይጠየቃሉ ያሉም ሲሆን አብረዋቸው ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የተጠረጠሩ ሁለት ኬንያውያን ጭምር በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚጠየቁም ገልጸዋል፡፡