"ጥቁሩ እየሱስ" በሚል በኬንያዊያን የሚታወቀው ይህ ግለሰብ ጉዳዩን እንዲያብራራ በፖሊስ ተጠርቷል
የኬንያ ፖሊስ ራሱን "እየሱስ ነኝ" ብሎ የሚጠራውን ግለሰብ ለማብራሪያ ጠራ።
ኢልዊድ ዌኬሳ በሚል ስሙ የሚጠራው ይህ ግለሰብ የአዲሷ እየሩሳሌም አዳኝ ነኝ በሚል ራሱን እየሱስ እንደሆነ በመናገር ላይ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።
- "ገነት አስገባችኋለሁ" በሚል ከአማኞች ገንዘብ የተቀበለው ናይጄሪያዊ ፓስተር ተከሰሰ
- አማኞች በረሃብ እንዲሞቱ አድርጓል የተባለው ኬንያዊ ፓስተር ፍርድ ቤት ቀረበ
በዚህ ጉዳይ ምርመራ እያደረገ የሚገኘው የኬንያ ፖሊስ አሁን ደግሞ ራሱን እየሱስ ክርስቶስ እያለ የሚጠራን ግለሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል።
በኬንያ አንድ ፓስተር አማኞች እየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት እንዲጾሙ እና በረሀብ እንዲሞቱ አድርጓል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
የፓስተር ፖል ማኬንዜ መልዕክትን ተቀብለው እየሱስን እናገኘዋለን በሚል ሲጾሙ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው እንደቀጠለ ነው ተብሏል።
በረሀብ የሞቱ ዜጎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ሲሆን እስካሁን 133 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
እንደ ፖሊስ ምርመራ ከሆነ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት ዜጎች የሰውነት አካል ጎድሎ መገኘቱ ጉዳዩ ከሀይማኖት ጋር ብቻ የተገናኘ ላይሆን ይችላል ተብሏል።
ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጉዳዩን የሚመረምር ልዩ ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን ይህ ኮሚሽንም ከ200 በላይ ዜጎችን ከከፋ ጉዳት መታደጉ ተገልጿል።