አሜሪካ እና አጋሮቿ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ለደረሱት 'ተኩስ አቁም ስምምነት' ተገዥ እንዲሆኑ እየሰሩ መሆኑን ገለጹ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሱዳን ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ለተኩስ አቁም ስምምነታቸው ተገዥ እንዲሆኑ ግፊት እየተደረገ ነው ብለዋል
በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት ከዚህ ቀደም የተደረሱት ስምምነቶች መጣሳቸው ይታወሳል
አሜሪካ ከሳኡዲ አረቢያ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት ጋር በመሆን የሱዳን ተፋላሚዎች የደረሱትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያራዝሙ እና እንዲተገብሩት እየሰራች መሆኑን አስታወቀች።
የሀግሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንደገለጹት፥ የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ የደረሱትን ተኩስ አቁም ስምምነት ተግብረው ለዜጎች ፈጣን የነፍስ አድን ድጋፍ እንዲቀርብ ግፊት እየተደረገ ነው።
ሚኒስትሩ ከብሪታንያ አቻቸው ጀምስ ክሌቨርሊ ጋር በሰጡት መግለጫ፥ የአሜሪካ እና የሳኡዲ ዲፕሎማቶች በጂዳ እየተካሄደ ባለው ድርድር “ጉልህ ተሳትፎ” እያደረጉ ነው ብለዋል።
ብሪታንያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች አጋሮችም የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲራዘም ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ነው አንቶኒ ብሊንከን ያብራሩት።
የሀገራቱ ጥረት ተፋላሚዎቹ በቀጣይ ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት ላይ የሚደርሱበትን ድርድር ማመቻቸት መሆኑንም አክለዋል።
ይሁን እንጂ ባለፈው እሁድ በሳኡዲ አረቢያ ጂዳ የተጀመረው ድርድር እስካሁን ምንም አይነት ስምምነት እንዳልተደረሰበት ተነግሯል።
የሱዳን ጦርም ሆነ የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤስኤፍ) የሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ነጻ መስመር እንዲኖር ፈቃደኝነታቸውን ከመግለጽ ውጭ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲራዘም ፍላጎት አላሳዩም ይላል የዘናሽናል ዘገባ።
አሜሪካ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ተፋላሚዎቹን በማደራደር ተደረሱ የተባሉት የተኩስ ማቆም ስምምነቶችም ወዲያውኑ መጣሳቸው አይዘነጋም።
በተያያዘ ቱርክ የሱዳን ተፋላሚዎችን ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል።
ከጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር በስልክ የተወያዩት ኤርዶሃን፥ አንካራ የሱዳን የሰላም ንግግሮችን ማስተናገድ እንደምትችል አንስተዋል።