አማኞች በረሃብ እንዲሞቱ አድርጓል የተባለው ኬንያዊ ፓስተር ፍርድ ቤት ቀረበ
በፓስተሩ “ከተራባችሁ ኢየሱስን ታገኛላችሁ” የሚል አስተምህሮ ሞተው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 109 ደርሷል
ይህን አስተምሮውን ተከትለው በጫካ ውስጥ ከምግብ ርቀው የተደበቁ ሰዎች ፍለጋ ሲካሄድ ሰንብቷል
በኬንያ በረሃብ ከጸናችሁ “ኢየሱስን ታዩታላችሁ፤ ገነትም ትገባላችሁ” በሚል አስተምሮው ከ100 በላይ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት የሆነው ፓስተር ፍርድ ቤት ቀረበ።
የ“ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች” መስራቹ ፓስተር ፖል ማኬንዚ በምስራቃዊ ኬንያ ማሊንዲ በተሰኘችው ከተማ ፍርድ ቤት መቅረቡን የኬንያው ሲቲዝን ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ፓስተር ፖል ማኬንዚ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 15 የአለም ፍጻሜ እንደሚሆን በመግለጽ ተከታዮቹ በረሃብ ራሳቸውን ገድለው ገነት ይገቡ ዘንድ መስበኩ ተጠቅሷል።
ይህን አስተምሮውን ተከትሎም በርካታ ተከታዮቹ ሻካሆላ ወደተባለ ጫካ መግባታቸውንና እስካሁን የ101 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን (አብዛኞቹ ህጻናት ናቸው) የኬንያ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ከ400 በላይ ሰዎችም የገቡበት አይታወቅም ያለው የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር በጫካው ውስጥ ለቀናት አሰሳ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።
በዚህም 8 ሰዎችን ማግኘት ቢቻልም ረሃብ አዳክሟቸው ብዙም ሳይቆዩ ህይወታቸው አልፏል ነው ያለው።
325 ሄክታር በሚሸፍነው ሻካሆላ ጫካ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር አሁንም በርካቶች በረሃብ ህይወታቸውን ሰውተው ፈጣሪያቸውን ለማየት እየተጠባበቁ እንደሚሆን ይገመታል።
በህይወት የተገኙትና ረሃብ ክፉኛ የጎዳቸው ሰዎችም ምግብ እንዲበሉ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱ ተነግሯል።
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያለውና ከዚህ ቀደምም በተለያየ ወንጀል ተይዞ በጉቦ የወጣው ማኬንዚ ስለቀረበበት ክስ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።
ሮይተርስ ግን ፓስተሩ ተከታዮቹን እንዲጾሙ አለማዘዙን መናገሩን የክስ ሂደቱን መርማሪዎች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ትናንት ፍርድ ቤት የቀረበው ፖል ማኬንዚ በጅምላ ተቀብረው በተገኙት ከ100 በላይ ሰዎች እና በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ክስ ይመሰረትበታል ተብሏል።