አንጋፋው የኬንያ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ለ5ኛ ጊዜ በእጩነት ቀረቡ
ኦዲንጋ ከምክትል ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥማቸውም ተጠብቋል
ኦዲንጋ ከቀድሞ ተቃናቃኛቸው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ድጋፍ እንዳገኙም ተነግሯል
አንጋፋው የኬንያ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ በሚቀጥለው ዓመት 2022 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ለ5ኛ ጊዜ በእጩነት መቅረባቸውን አስታውቀዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ከቀድሞ ተቃናቃኛቸው ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ያደረጉትን ድንገተኛ የእርቅ ስምምነት ተከትሎ ለወራት የቆየውን ጥርጣሬ አሁን ላይ እንዳረገበው ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ራይላ ኦዲንጋ እጩነትም ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ድጋፍ ማግኘቱም ነው የተገለፀው።
የ76 ዓመቱ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ በናይሮቢ ስታዲየም በፖለቲካ ታጋዮች እና በሺዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎቸ በተገኙበት ነው ለፕሬዝዳንትንት እንደሚወዳደሩ ይፋ ያደረጉት።
ለበርካታ አስርት አመታት የኬንያ ተቃዋሚዎች መለያ ሆነው ያገለገሉት ራይላ ኦዲንጋ ከኬንያታ ጋር የስልጣን መጋራት ስምምነት ማድረጋቸው አሁን ላይ ለፕሬዝዳንትነት የሚያደርጉትን ጉዞ ሊያግዛቸው እንደሚችልም ግምት ተሰጥቷል።
ኦዲንጋ በደጋፊዎቻቸው ፊት ባደረጉት ንግግር “በአውሮፓውያ ነሐሴ 9 ቀን 2022 ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እራሴን እንደ ፕሬዚዳንታዊ እጩ አቅርቤአለሁ” ብለዋል።
“በህይወታችን ዲሞክራሲያዊ እና ተራማጅ ኬንያን ለመገንባት ቁርጠኛ ነኝ” ሲሉም ኦዲንጋ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ተንታኝ ኔሪማ ዋኮ-ኦጂዋ ለፈረንሳዩ የዜና ወል /ኤ.ኤፍ.ፒ/ እንደተናገሩት "በኦዲንጋ እና ዊልያም ሩቶ መካከል ጠንካራ ፉክክር ይኖራል፤ ከሁለቱ አንዱ የዱላውን መቀበሉ የማይቀር ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት የ54 ዓመቱ ዊልያም ሩቶ አሁን ያለውን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና በ"ስርወ መንግስት" በምትመራው ሀገር፤ ኑሯቸውን ለመምራት ለሚጥሩ "አሳዳጊዎች" ጥቅም ለመቆም ሲሉ እራሳቸውን እንደ መሪ አስቀምጠዋል።
ኬንያ እንደፈረንጆቹ 1963 ነፃነቷን ከጸቀዳጀች በኋላ የኬንያታ እና የኦዲንጋ ቤተሰቦች የኬንያ ፖለቲካን ተቆጣጥረው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
ኦዲንጋ በመስከረም ወር ከኤ.ኤፍ.ፒ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ምርጫውን የማሸነፍ አቅም እንዳላቸው” በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
እንደ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር እድሉን ካገኘሁ ብዙ ለውጦችን ማምጣት እችላለሁ ያሉት ኦዲንጋ፤"ኬንያውያንን በደንብ የመረዳት የካበተ ልምድ አለኝ" ማለታቸውንም የሚታወስ ነው።