ኬንያ በሁለተኛ ዙር ምርጫ ጁቡቲን በማሸነፍ ቋሚ ያልሆነ የተመድን ጸጥታ ምክርቤት መቀመጫ አሸነፈች
ኬንያ በሁለተኛ ዙር ምርጫ ጁቡቲን በማሸነፍ ቋሚ ያልሆነ የተመድን ጸጥታ ምክርቤት መቀመጫ አሸነፈች
ኬንያ ጅቡቲን በሁለተኛ ዙር ምርጫ 129 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምጽ በማሸነፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) የጸጥታ ምክርቤት ቋሚ ያልሆነ መቀመጫ ማሸነፍ ችላለች፡፡
በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ኬንያ አብላጫ ድምጽ ማግኜት ባለመቻሏ ነበር ሁለተኛ ዙር ምርጫ ማድረግ ያስፈለገው፡፡
ኬንያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት ያሉት የኬንያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ የዲሞክራሲና ከብዙ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አውስተው ነበር፡፡ፕሬዘዳንቱ ኬንያ የምታሸንፍ ከሆነ የአፍሪካን አጀንዳ ወደ ፊት እንዲመጣና አለምአቀፍ ወንድማማችነት እንዲጎለብት እንደምትሰራም ገልጸው ነበር፡፡
ሜክሲኮ፣ ህንድ፤አየርላንድና ኖርዌይ ባለፈው እሮብ እለት የተመረጡ ሲሆን ኬንያ ደግሞ በዛሬው እለት ማሸነፏ ተረጋግጧል፡፡ ሀገራቱ 15 አባላት ባሉት የጸጥታው ምክርቤት ሁለት አመት የሚቆይ ስልጣን የሚኖራቸው ሲሆን ስልጣናቸውን በፈረንጆቹ 2021 ስልጣን ይረከባሉ፡፡
ሜክሲኮና ህንድ ያለተቀናቃኝ ያሸነፉ ሲሆን አየርላንድና ኖርዌይ ካናዳን በማሸነፍ ነው የተመረጡት፡፡ የአህጉራዊ ውክልናን ለማመጣጠን መቀመጫዎች በሪጀናል ቡድን የተካፋፈሉ ናቸው፡፡ሁሉም እጩዎች ለማሸነፍ የጠቅላላ ጉባኤውን 2/3 ድምጽ ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ኬንያም ሆነች ጅቡቲ በመጀመሪያው ዙር ማሸነፍ አልቻሉም ነበር፡፡
ከመጋቢት ወር ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በኦንላይ ስራቸውን ሲሰሩ የነበሩ ዲፕሎማቶች እሮብ እለት ወደ ጠቅላላ ጉባኤው አዳራሽ በመግባት በሚስጥር ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
የጸጥታው ምክርቤት ማእቀብ መጣልንና ሀይል መጠቀምን ጨምሮ ትላልቅ ገዥ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ ብቸኛ የተመድ አከል ነው፡፡