ኬንያ እና ኡጋንዳ አለመግባባት ውስጥ የገቡትን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ሊያሸማግሉ መሆኑን ሩቶ ተናገሩ
ሩቶ ይህን ያሉት በቀጣናዊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ነው

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመገንባት የተፈራረመችው ስምምነት ሞቃዲሹን አስቆጥቷል
ኬንያ እና ኡጋንዳ አለመግባባት ውስጥ የገቡትን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ሊያሸማግሉ መሆኑን ሩቶ ተናገሩ።
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ከኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዮሪ ሙሴቬኒ ጋር በመሆን ኢትዮጰያ እና ሶማሊያ የአፍሪካ ቀንድን ወደ አለመጋጋት ውስጥ ሊከት የሚችለውን ችግር በውይይት እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርጉ በትናንትናው እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሶማሊያ ውስጥ አልሸባብን እየተዋጉ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ያላት ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመገንባት የተፈራረመችው ስምምነት ሞቃዲሹን አስቆጥቷል።
ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ በ50 አመት የሊዝ ኪራይ ለመስጠት የተስማማችው፣ ኢትዮጵያ በምላሹ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጣት በመፈለግ ነበር።
ሶማሊላንድ በምርጫ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የምታደርግ እና ነጻነቷን ካወጀችበት ከ1991 ጀምሮ በአንጻራዊነት ሰላማዊ እና የተረጋጋች ብትሆንም አለምአቀፋዊ የሀገርነት እውቅና ማግኘት አልቻለችም።
ይህ ፍጥጫ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለው ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ለገባችው ግብጽ እንድትቀርብ አድርጓታል።
"የሶማሊያ ሰላም መሆን ለቀጣናው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጵኦ ስለሚኖረው እና ቀጣናው ለኢንቨስትመንት የተመቸ እንዲሆን ያደርጋል" ብለዋል ሩቶ በቀጣናዊ የሀገራት መሪዎች ስብሰባ ላይ በሰጡት መግለጫ።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በቱርክ አንካራ የተደረጉ በርካታ ንግግሮች ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መፍትሄ አላመጡም።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሸክ ሞሀሙድ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ሞሀሙድ ከስብሰባው ጎንለጎን ከሩቶ እና ሙሴቬኒ ጋር መገናኘታቸውን ገልጿል፤ ነገርግን ስለንግግሩ ጉዳይ ምንም አላለም።
የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በቀጣናዊ መሪዎች የሚቀርቡ የመፍትሄ ሀሳቦች በአዲስ አበባ በኩል ተቀባይነት አለማግኘታቸውን እና በቱርክ እየተካሄደ ያለው ንግግር ፍሬያማ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ቀደም ሲል ለሮይተርስ ተናግረዋል።
በሮይተርስ በዚህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የገባችው ስምምነት የማንንም ፍላጎት የማይጻረር መሆኑን እና የተፈጠረውን አለመግባባትም በውይይት ለመፍታት እንደምትፈለግ በተደጋጋሚ ገልጻለች።