ኢራን በሶሪያ አሌፖ የሚገኘው ቆንስላዋ የሽብር ጥቃት እንደተፈጸመበት ገለጸች
በጥቃቱ በዲፕሎማቶቿ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ያስታወቀችው ቴህራን ጠንካራ የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች

ሃያት ታህሪር አል ሻም የተሰኘው አማጺ ቡድን የአሌፖ ከተማን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠሩ ተነገሯል
ኢራን በሶሪያ አሌፖ የሚገኘው ቆንስላዋ የሽብር ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታወቀች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባግሄ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በቆንስላው ህንጻ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የ1963ቱን የቬይና ኮንቬንሽን የጣሰ ነው ብለዋል።
በጥቃቱ ቆንስላ ጀነራሉም ሆኑ ሌሎች ዲፕሎማቶች ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የገለጹት ቃል አቀባዩ፥ በህንጻው ላይ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር አላብራሩም።
የሽብር ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ሳይጠቅሱም "ጠንካራ የአጻፋ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ዝተዋል።
ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ ከሶሪያ ጦር ጋር ሲዋጋ የቆየው ሃያት ታህሪር አል ሻም የተሰኘው አማጺ ቡድን የአሌፖ ከተማን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠሩ ተገልጿል።
"ጀብሃት አል ኑስራ" ወይም "ኑስራ ፍሮንት" በሚል ስያሜው የሚታወቀው አማጺ ቡድን በ2016 በሶሪያ ጦር የተነጠቀውን አሌፖ ዳግም መቆጣጠሩን የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው።
ኢራን እና ሩሲያ የሚደግፉት የሶሪያ መንግስት ጦርም ለመልሶ ማጥቃት በሚገባ ለመደራጀት በሚል ከከተማዋ መውጣቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ ለበሽር አል አሳድ ጦር ከለላ ለመስጠት በአማጺ ቡድኑ ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው ፤ በሶስት ቀናት ውስጥ ለደማስቆ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል መግባቷም ተሰምቷል።
በአሌፖ የሚገኘው ኤምባሲዋ የሽብር ጥቃት እንደተፈጸመበት የገለጸችው ቴህራን ከ2011 ጀምሮ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በገባችው ሶሪያ የአሳድ ደጋፊ እንደነበረች ይታወሳል።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የአማጺያኑ ጥቃት የእስራኤል እና አሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን የማተራመስ እቅድ አካል ነው ብለውታል።
ቴህራን በቀጣይ ለሶሪያ ጦር ምን አይነት ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ሶሪያ ለአመታት በጦርነት ውስጥ ለመቀጠሏ የሩሲያ እና ኢራን ጥገኛ መሆንን በምክንያትነት የምታነሳው ዋሽንግተን በበኩሏ ከአሁኑ "ሃያት ታህሪር አል ሻም" ጥቃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ብላለች።
የበሽር አል አሳድ መንግስት ለፖለቲካዊ ንግግር ራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቧንም አርቲ ዘግቧል።