"ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር ሰላም ካልፈጠረች ለቀጠናዊ መረጋጋት አዎንታዊ ሚና አይኖራትም" - ፕሬዝዳንት ኢሳያስ
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና ኤርትራ ከሶማሊያ እና ግብጽ ጋር ስለተፈራረመችው የሶስትዮሽ ስምምነት ማብራሪያ ሰጥተዋል

የትራምፕ "አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናደርጋለን" መፈክርም የአሜሪካን ልዕለ ሃያልነት እየተዳከመ መምጣት ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ቃለምልልስ ሰጥተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ እና ህወሃት፣ ኤርትራ ከሶማሊያ እና ግብጽ ጋር ስለተፈራረመችው የሶስትዮሽ የደህንነት ስምምነት፣ በሱዳን ጦርነት እና በትራምፕ ዳግም መመረጥ ዙሪያ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
በኢትዮጵያ እና ህወሃት ዙሪያ ምን አሉ?
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ግጭትና ከጎረቤቶቿ ጋር አለመስማማት ውስጥ የሚከታት በ1987 ዓ.ም ያጸደቀችው "ብሄር ተኮርና ተቋማዊ አሰራርን የዘረጋ" ህገመንግስት ነው ብለዋል።
ህገመንግስቱ "ውጥረት ከመፍጠር ባሻገር የሀገር ግንባታን የማያበረታታ ነው፤ ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር ሰላም ካልሆነች ለቀጠናው መረጋጋትና ትብብር አዎንታዊ ሚና አይኖራትም" ሲሉ መናገራቸውንም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሻባይት በተሰኘ በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነት ውስጥ የገቡት፤ በባድሜም ለሁለት አስርት ሰፍኖ የቆየው ውጥረትም "የተሳሳተው የኢትዮጵያ ፖሊሲ" ውጤት ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፥ ለሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብና ጦርነት የውጭ ሃይሎች (በስም ያልጠቀሷቸው) ጣልቃገብነት እንደነበር አብራርተዋል።
አስመራ እና አዲስ አበባ ጦርነቱን በስምምነት ከቋጩ በኋላም ሆነ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የቀጠለው ግጭትና ጦርነት መነሻንም ከህገመንግስቱ ጋር አያይዘውታል።
"ህወሃት የሪፎርም አጀንዳዎችን ወደጎን በመተውና ጦርነት በመምረጥ ወደ ኤርትራ ከ70 በላይ ረጅም ርቀት ሮኬቶችን ተኩሷል፤ ህወሃት ይህን ድርጊት እንዲያቆም ያቀረብነው ጥያቄ ሰሚ አላገኘም ነበር" ሲሉ ያወሳሉ።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በአማራ ክልል አዲስ ግጭት መከሰቱን በመጥቀስም "ወደ ክሶችና ወቀሳዎች መግባት አንፈልግም፤ ዋናው ትኩረታችን ሁሌም ደም አፋሳሽ ጦርነትን መከላከል እና ማስወገድ ነው" ብለዋል። መንግስታቸው ላይ የሚነሳውን ወቀሳ እንደማይቀበሉትም ተናግረዋል።
በኤርትራ፣ ግብጽ እና ሶማሊያ የትብብር ስምምነት
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ፣ ግብጽና ሶማሊያ በጥቅምት ወር መጀመሪያ በደረሱት የሶስትዮሽ የደህንነት ትብብር ዙሪያ የተዛቡ መረጃዎች ሲወጡ መክረማቸውን አንስተዋል።
"የውጭ ሀይሎች በመደበኛ እና ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እያሰራጩት ያለው የተዛባ መረጃ በቀጠናው ግጭት ያባብሳል፤ ዘገባዎቹ ለኢትዮጵያ ከልብ በማሰብ የሚሰሩ አይደሉም " ሲሉም ገልጸዋል።
የሶስትዮሽ ስምምነቱን አዎንታዊ እና ትክክለኛ ጉዳዮች ሆን ብሎ የማውጣት ዘመቻ ስለነበር ቀጠናዊ መረጋጋት ለማስፈን ስምምነት የደረስንባቸው ነጥቦች እንዲሸፈኑ ሆኗልም ነው ያሉት።
"ኤርትራ በየትኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያን ያለመረጋጋት ውስጥ የመክተት ፍላጎት የላትም፤ በአፍሪካ ቀንድ፣ በናይል ተፋሰስ እና ቀይ ባህር ዙሪያ ትብብርን ማጠናከርና መረጋጋትን ማስፈን ጽኑ ፍላጎት አለን" ሲሉም አክለዋል።
በቀጠናው ሀገራት መካከል የሚደረጉ ምክክሮች አለመተማመንን እንደሚያስወግዱና በተዋዋይ ወገኖች መካከል አዎንታዊ እና ፍሬያማ መስተጋብር ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩም ጠቅሰዋል።
የሱዳን ጦርነት
ሃይማኖታዊ ፍላጎትና የውጭ ሃይሎች ጣልቃገብነት ሱዳንን ከ2019 ጀምሮ ጦርነት ውስጥ መክተቱን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናግረዋል።
የሱዳን ግጭት በዋናነት የሚፈታው በሀገሪቱ ህዝብ ቢሆንም ኤርትራ ከሱዳን ጋር ካላት ታሪካዊ ግንኙነት አንጻርና የአፍሪካ ቀንድን መረጋጋት ከመሻታችን የበኩላችን ሚና መጫወት ይኖርብናል ብለዋል።
በዚህም ኤርትራ በ2022 አጋማሽ "አጨቃጫቂ ያልሆነና በብዙሃኑ ተቀባይነት ያገኘ ምክረሃሳብ" አቅርባ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በውጭ ሃይሎች ጣልቃገብነት የቀጠለው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።
በትራምፕ ዳግም መመረጥ
የኤርትራው ፕሬዝዳንት በአሜሪካ በቅርቡ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኤርትራ እና በአፍሪካ ስለሚኖረው ተጽዕኖም ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
የትራምፕ "አሜሪካን ዳግም ታላቅ እናደርጋለን" መፈክር የአሜሪካን ልዕለ ሃያልነት መዳከምን እና የባለአንድ ወገን የአለም ስርአት እያከተመለት መሆኑን ያሳያል ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፥ አሜሪካ በምጣኔ ሃብት፣ ወታደራዊ፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች ተጽዕኖዋ መቀነሱን አብራርተዋል።
ቻይና እና ሩሲያ በምጣኔ ሃብት እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሜሪካን እየተገዳደረ መሆኑን በማንሳትም የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፖሊሲ ለውጥ ያመጣል ወይ የሚለው አጠራጣሪ መሆኑን ተናግረዋል።
በትራምፕ ፖሊሲዎች ዙሪያ ድምዳሜ ለመስጠት ጊዜው ገና ቢሆንም "የቤት ስራችን እየሰራን ገንቢ ለሆነ ግንኙነት መዘጋጀት ይኖርብናል" ሲሉ መናገራቸውንም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረገጹ አስፍሯል።