በነገው እለት በዋና ከተማዋ እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ ጠሪ ተላልፏል
አዲስ የፋይናንስ ህግን በመቃዎም በኬንያ በመካሄድ ላይ የሚገኝው ህዝባዊ ተቃውሞ በርትቶ ቀጥሏል፡፡
የተለያዩ ግብር ጭማሪዎችን ገቢራዊ ለማድረግ አቅዶ የነበረውን የኬንያ የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ውድቅ ቢያደርጉትም ተቃውሞው ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ይልቀቁ ወደ ሚል ከፍተኛ አመጽ ተቀይሯል።
በሀገሪቱ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ፓርላማው ያጸደቀው ረቂቅ ሕግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ወጣቶች እንዲረጋጉ እና ለወይይት እንዲቀመጡ ጥሪ ቢያቀርቡም ኬንያውያን ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሶስት ሳምንታትን አስቆጥረዋል፡፡
የኬንያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተቃውሞ ሰልፎቹን ለማብረድ የተሰማሩ ፖሊሶች በከፈቱት ተኩስ እስካሁን የ39 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አድርጓል፡፡
ባሳለፍነው እሁድ ከጋዜጠኞች ጋር ስለ ጉዳዩ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሩቶ በበኩላቸው የሟቾችን ቁጥር ወደ 19 ዝቅ አድርገውታል፡፡
በትላንትናው እለት በኤክስ (ትዊተር) ገጽ ላይ በቀጥታ በተደረገ ይፋዊ የህዝብ ውይይት 400ሺህ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ተቃውሞው መቀጠል እንዳለበት በርካታ ተሳታፊዎች ሀሳብ ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞውን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እና በተለያዩ መንገዶች እያስተባበሩ የሚገኙ የማህበረሰብ አንቂዎች በበኩላቸው ወደ መደብሮች ዝርፍያ እና አመጻ የተቀየረውን ተቃውሞ እንዴት ወደ ሰላማዊ ትግል እንመልሰው በሚለው ጉዳይ ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
በተቃውሞዎቹ አካሄድ ላይ የስትራቴጂ ለውጥ ያለፈልገናል ያሉት የማህበረሰብ አንቂዎች ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰልፎችን ለመጥለፍ ዘራፊ እና ሌቦችን በመካከላችን ስላሰማሩ ይህን ማጽዳት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ትላንት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በርካታ መደብር ሱቆች እና መኖርያቤቶች የዝርፍያ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ሮይተርስ ያነጋገረው ተቃውሞውን ከሚመሩት የማህበረሰብ አንቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ኦጃንጎ ኦሞንዲ “ዊሊያም ሩቶ ከስልጣን እስከሚነሱ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፤ ነገር ግን ትግሉን ወዳልሆነ አቅጣጫ የሚወስዱ በመካከላችን የሚገኙ አካላትን ለማጥራት ነገ ሊደረግ የታቀደውን ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘግየት እየተነጋገርን ነው” ብሏል፡፡
አክሎም “ይህ የማይሆን ከሆነ ፖሊስ እንዲገድለን ተጨማሪ እድል እየሰጠነው እንደሆነ መታወቅ አለበት” ነው ያለው፡፡
የታክስ ህጉን በአደባባይ መቃወም በተጀመረበቸው የመጀመሪያ ቀናት ሰልፈኞች መፈክሮችን በመያዝ ብቻ ሰላማዊ ሰልፎችን ያደርጉ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዱላ ፣ ብረት እና ዲንጋይ ይዘው የሚታዩ ሰልፈኞች ቁጥር መጨመር ተቃውሞው ወደለየለት አመጽ እንዳይቀየር አስግቷል፡፡
የኬንያ ፖሊስ የትላንቱን ዝርፍያ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ከእንግዲህ እንደማይታገስ ህግን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው እሁድ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ደረጉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በፋይናንስ ሕጉ በሚጣሉ ተጨማሪ ግብሮች 350 ቢሊዮን ሽልንግ ለማሰባሰብ እና አገሪቱም 600 ቢሊዮን ሽልንግ ለመበደር አስባ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኬንያ በአሁኑ ወቅት ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ አማራጭ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡