የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መሥራችና ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ መኮንን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣን በመምራት ተወዳጅ ካደረጓት በቀዳሚነት ይጠቀሳል
ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ ረፋዱ ላይ ህይወቱ አልፏል
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መሥራቾች አንዱ የሆነው ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ህይወቱ ማለፉን አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስታውቋል።
ነቢይ መኮንን ከአዲስ አድማስ መሥራቾች አንዱ የሆነውና በዋና አዘጋጅነት ጋዜጣዋን በመምራት “ተወዳጅ ካደረጓት በቀዳሚነት” ስሙ እንደሚነሳም አድማስ ጋዜጣ አስታውቋል።
ነቢይ መኮንን በህትመት ሚዲያ ዘርፍ ዋና አዘጋጅነትን ጨምሮ በርካታ በነበረው አገልግሎት የተለያዩ ስራዎቹን ለአንባቢያን አድርሷል።
ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን፤ “ስውር ስፌት” ቁጥር አንድና ሁለት፣ የግጥም መድበሎችን ጨምሮ በርካታ የግጥም ስራዎችን በተለያዩ መድረኮች በማቅረብ ይታወቃል፡፡
“የኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፉም ተጠቃሽ ስራው ነው፡፡
ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን “Gone With The Wind” የተሰኘውን በአሜሪካዊቷ ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል የተደረሰውን ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ተርጉሞ አስነብቧል፡፡