በጸጥታ ሀይሎች ጫናዎች ምክንያት የአማራ ክልል ህዝብ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ተደርጓል- ሂዩማን ራይትስ ዋች
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳላየ መሆናቸውን እንዲያቆሙም ተቋሙ አሳስቧል
በክልሉ የተሰማሩ ወታደሮች የሕክምና ባለሙያዎችን የፋኖ ዶክተር ናችሁ በሚል እያንገላቱ መሆኑን ተቋሙ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል
በጸጥታ ሀይሎች ጫናዎች ምክንያት የአማራ ክልል ህዝብ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ተደርጓል- ሂዩማን ራይትስ ዋች፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዋች በኢትዮጵያ አማራ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ አዲስ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
የተቋሙ ሪፖርት ካሳለፍነው ነሀሴ 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 2016 ዓ.ም ባሉት 10 ወራት ውስጥ ተፈጽመዋል ባለቸው ጉዳዮች ዙሪያ አተኩሯል፡፡
በአማራ ክልል ከጤና እና ተያያዥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ያተኮረው ይህ ሪፖርት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የጤና ተቋማትን ኢላማ አድርገዋል ብሏል፡፡
ተቋሙ 58 ተጎጂዎችን እና የአይን ምስክሮችን ቃለ መጠይቅ አድርጌ አወጣሁት ባለው ሪፖርቱ ላይ እንዳለው ወታደሮች ለህክምና ወደ ሆስፒታል ሲገቡ ቢሞቱ ሐኪሞቹ ተጠያቂ እንደሚሆኑ እንደሚነገራቸው እና ጫና ውስጥ እንደሚገቡ ጠቅሷል፡፡
ህመምተኞችን የጫኑ አምቡላንሶች እና የህክምና ቁሳቁሶች በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች መውደማቸውን የገለጸው ተቋሙ ተቋሙ በህክም ባለሙያዎችም ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ወታደሮች የህክምና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት እየገቡ ገልግሎቱን እንደሚያቋርጡ፣ የቆሰሉ የፋኖ ታጣቂዎችን እንዳያክሙ እና ያልተገቡ ከህግ ውጪ የሆኑ እስር እና ድብደባ እንደሚፈጽሙም ተቋሙ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
የጸጥታ ሀይሎች ከህክምና ባለፈ የሰብዓዊ መብት ድጋፍ ስራዎች ላይ ጣልቃ በመግባት የአማር ክልል ህዝብ ከሰብዓዊ ድጋፍ ውጪ እንዲሆን እያደረጉ ነውም ብሏል፡፡
በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያበቃም ክልሉ አሁንም በኮማንድ ፖስት እየተመራ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
የሕክምና ባለሙያዎችን በወታደራዊ ማዘዣ ካምፖች እና ጣቢያዎች ውስጥ ማሰር፣ ማስፈራራት እና እናንተ የፋኖ ዶክተር ናችሁ ብሎ መፈረጅን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቶችን ሲያደርስ ነበር ሲልም ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ሀይሎች በህክምና ላይ የነበሩ ታካሚዎችን የፋኖ ታጣቂዎች ናችሁ፣ ግንኙነት አላችሁ በሚል ከህክምና ቦታዎች ላይ እንደሚወስድ ይህም ታካሚዎች በፍርሃት ወደ ጤና ተቋማት እንዳይመጡ እና ሌሎች ጉዳቶች እንዲጋለጡ እያደረገ ነውም ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ እያለ የኢትዮጵያ አጋር የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥሰቱን እንዳላየ ሆነዋ ሲል ኮንኗል፡፡
በተለይም የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም አጋር አካላት በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያወግዙ ሒዩማን ራይትስ ዋች አሳስቧል፡፡
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት የተጀመረው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ግዕት እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ በክልሉ ለ10 ወራት የቆየ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የነበረ ሲሆን ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ይህ አዋጅ ጊዜው ቢያበቃም ክልሉ ወደ ቀድሞ ሲቪል አስተዳድር አልተመለሰም፡፡