ኬንያዊው የአለም ሪከርድ ባለቤት አትሌት ለ6 አመታት ከየትኛውም ውድድር ታገደ
ሮኒክስ ኪፕሩቶ የተባለው አትሌት አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅሟል በሚል ነው ከውድድር የታገደው
ከ2015 እስከ 2022 ድረስ 300 የኬንያ አትሌቶች ከአበረታች ንጥረነገር ጋር በተያያዘ የተለያየ ቅጣት ተላልፎባቸዋል
ኬንያዊው የ24 አመት ሯጭ ሮኔክስ ኪፕሩቶ ከአበራታች ንጥረ ነገር (ዶፒንግ) አጠቃቀም ጋር በተገናኘ በምርመራ በተገኝበት ውጤት ለ6 አመታት ከየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር ውጭ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ኪፕሩቶ በ2020 በቫሌንሲያ በተካሄደው የአለም ሻምፒዮና በ10 ኪሎሜትር ማራቶን ውድድር የርቀቱን ክብረወሰን በማሻሻል ማሸነፉ ይታወሳል።
አትሌቱ በ2019 በስቶክሆልም ዳይመንድ ሊግ የ10ሺ ሜትር አሸናፊም ነበር፡፡
ከአበረታች ንጥረነገር አጠቃቀም ጋር በተገናኘ በባለፈው አመት ከውድድር ታግዶ የነበረው አትሌቱ በመጨረሻም ለ6 አመታት በየትኛውም ውድድር እንዳይሳተፍ ክልከላ ተጥሎበታል፡፡
በተጨማሪም የ10 ኪሎሜትር ማራቶን ሪከርዱን ጨምሮ አትሌቱ ያሸነፋቸው ሜዳሊያዎችን እንደሚነጠቅ ነው የተሰማው።
ኤአይዩ የተባለው በአትሌቱ ላይ ምርመራ ሲያደርግ የነበረው አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋም ኪፕሩቶ በ2019ኙ የስቶክሆልም ዳይመንድ ሊግ ውድድር በሰውነቱ ውስጥ የተወሰደ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅሞ ነበር ብሏል፡፡
ምንም እንኳን አትሌቱ ግኝቱ የተሳሳተ መሆኑን ከደም ዝውውር እና ከአካባቢ መቀያየር ጋር የተገናኘ እንጂ ሆን ብሎ የወሰደው አበረታች ንጥረ ነገር አለመኖሩን ቢናገርም የውሳኔው ተፈጻሚነት አይቀሬ ነው ተብሏል፡፡
ኬንያዊያን አትሌቶች ከአበረታች ንጥረነገሮች ጋር በተገናኘ ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል።
ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2022 ድረስ 300 የኬንያ አትሌቶች ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ የተለያየ ቅጣት እንደተላለፈባቸው የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
በ2022 ብቻ 27 ኬንያዊያን አትሌቶች ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል ተብሏል።