ኬንያዊቷ ነርስ የ250 ሺህ ዶላር ሽልማት አሸነፈች
ዓለም አቀፉ የነርሶች ቀን ትናንት በዱባይ ተከብሯል
ኬንያዊቷ ነርስ የ250 ሺህ ዶላር ሽልማት አሸነፈች
ነርስ አና ካባሌ ዱባ ኬንያዊት ስትሆን በመርሳቢት ሪፈራል ሆስፒታል በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ይህች ነርስ በምትኖርባቸው አካባዎች የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡
እነዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ማህበረሰቡን ማስተማር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ካባሊ ዱባ ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም በመመስረት ሰዎች አመለካከታቸውን መቀየር የሚያስችሉ ስራዎችን ስትሰራም ነበር፡፡
ዓለም አቀፉ የነርሶች ቀን በትናንትናው እለት በአረብ ኢምሬትስ በተከበረበት ወቅት ይህቺ ነርስ የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሴቶችን እና ህጻናትን የሚጎዱ ድርጊቶችን ለመከላከል ላደረገችው ጥረት እውቅና ተሰጥቷታል፡፡
ነርስ አና ካባሌ ለጥረቷ የ250 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደተበረከተላትም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ 28 ሀገራት የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክል ህግ ያወጡ ቢሆንም በነዚህ ሀገራት ውስጥ 55 ሚሊዬን ሴት ህጻናት መገረዛቸውን የዓለም ህጻናት አድን ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው ጥናታዊ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ሶማሊያ፣ጊኒ፣ጅቡቲ፣ማሊ፣ግብጽ፣ ሱዳን እና ሴራሊዮን በአፍሪካ ከ80 በመቶ በላይ ሴቶቻቸው ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ 65 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እንደሚገረዙ የዘሁ ተቋም ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ዛምቢያ፣ኒጀር፣ዩጋንዳ፣ዚምባብዌ፣ጋና እና ቶጎ ደግሞ በአፍሪካ የሴት ልጅ ግርዛት በአንጻራዊነት የማይፈጸምባቸው ሀገራ እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡