ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶን “ስልጣን ልቀቅ” አሉ
ዊሊያም ሩቶ ኬንያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ እንድትወጣ የሚጠበቅባቸውን አልሰሩም በሚል ነው የተወቀሱት
የሁለቱ ውዝግብ እየተካረረበ የመጣው ነሃሴ ወር ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ተነግሯል
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው እንዲለቁ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸው የሆኑት ዊሊያም ሩቶ “ኬንያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ እንድትወጣ የሚጠበቅባቸውን አልሰሩም” በሚል ይከሷቸዋል።
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግስትን ከውስጥ ሆነው መተቸት እንደሌለባቸውም ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዚደንት ሩቶ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኬንያ መንግስት ካቢኔ ተሰብስቦ እንደማያውቅ እና የመንግስት ውሳኔዎች በፐሬዝዳንቱ የስልክ ጥሪ ብቻ እንደሚተላለፉ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ኬንያ የፊታችን ነሃሴ ወር ላይ ከምታደርገው በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት በሁለቱ መካከል ያለው የከረረ አለመግባባት ይፋ መውጣቱ ተነግሯል።
በፕሬዝዳንቱ እና በምክትል ፕሬዝዳንቱ መካከል ያለው ልዩነት ገሃድ የወጣውም የሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሞዋይ ኪባኪ ሞትን ተከትሎ በነበረው የሀዘን ስነ ስርዓት ላይ ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በነበረው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ስርዓተ ቀብር ላይም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን እጅ ለመጨበት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ተመልክቷል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸውን ከኃላፊነት የማባረር ስልጣን የላቸውም የተባለ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ከስልጣን ሊነሳ የሚችለው ከተከሰሰ ወይም አቅም ከሌለው ብቻ ነው።
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፊታችን ነሃሴ ወር በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በእጩነት መቅረባቸው ይታወሳል።
የስልጠን ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ክምክትላቸው ይልቅ ለቀድሞ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “ማንንም መደገፍ መብታቸው ነው፤ ምርጫውን ግን እኛ እናሸንፋለን” ሲሉ ተደምጠው ነበር።
የኡሁሩ ኬንያታ እና የዊሊያም ሩቶ አለመግባባት መነሻም የፊታችን ነሃሴ ወር የሚካሄደው ምርጫ ጉዳይ ሳይሆን እንዳልቀረ መላ ምቶች ተቀምጠዋል።