አፍሪካ በ2030 ወባን ለማጥፋት እየሄደችበት ያለው ፍጥነት ደካማ መሆኑን የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ገለጹ
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ 96 በመቶ የዓለም የወባ በሽታ የሚከሰቱት በአፍሪካ አህጉር ላይ ነው
በፈረንጆቹ 2020 ብቻ 611 ሺ 802 አፍሪካውያን በወባ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ
አፍሪካ በፈረንጆቹ 2030 ወባን ለማጥፋት እየሄደችበት ያለ ፍጥነት ደካማ መሆኑን የአፍሪካ መሪዎች የወባ ጉዳዮች ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት ከሆነ “አፍሪካውያን እንደፈረንጆቹ በ2020 የወባ በሽታን እና ሞትን በ 40 በመቶ የመቀነስ ግባቸው እንኳን ማሳካት አልቻሉም” ሲሉ ተናግሯል።
ይልቁንም እንደፈረንጆቹ “ከ2015 እስከ 2020 በነበሩ ዓመታት ማሳካት የተቻለው 1በመቶ በቻ ነው” ሲሉም አክሏል፡፡
ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ 2030 የታየዘውን ወባን የማስቆም ግብ እውን ለማድረግ የአፍሪካ መሪዎች ቆራጥ እርምጃ እንደሚስፈልግም አሳስቧል፡፡
አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ወባ የሚስተዋልባቸው 10 ሀገራት በ "ሃይ በርደን ፎር ሃይ ኢምፓክት" አቀራረብ ስልቶችን በመተግበር ላይ መሆናቸው ከአፍሪካ ህብረት የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ማሊ እና ናሚቢያ የመሳሰሉ ሀገራት “ማላሪያን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል” የሚል ሀገር አቀፍ ዘመቻ የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ ዘመቻው የተቀላቀሉት ሀገራት ቁጥር ወደ 23 አባል ሀገራት ማሻቀቡ ተገልጿል፡፡