ጉባዔው ግጭትና ጦርነትን ሊያስቀሩ እና ምቹ የልማት መደላድሎችን ሊፈጥሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራል
የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ጉባዔ ተጀመረ
33ኛው የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ጉባዔ የህብረቱ አባል ሃገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሚሳተፉበት 36ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
ጉባዔው “ግጭትና ጦርነትን በማስቀረት ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታዎችን እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን አባል ሃገራቱ በመተባበር የሽብር ምንጭ የሆነውን ግጭት ማስቆም እንደሚገባቸው የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡
ህብረቱ ግጭትና ጦርነትን በማስቀረት ምቹ የልማት ሁኔታዎችን ለመፍጠር የጀመረው ጥረት የሚሳካው በአባል ሃገራቱ ቁርጠኛነትና ትብብር መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽን ለቀመንበሩ ሃገራትን ማሳመንን ጨምሮ አድካሚና ውስብስብ ሂደቶችን ያለፈው አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የመፍጠር ሂደት ወደ ትግበራ ለመግባት ከሚያስችል የመጨረሻ ሂደት ላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስን መሰል ድንበር ዘለል ወረርሽኞች ለመከላከል የሚቻልበትን መላ ህብረቱ እንደሚዘይድም ነው የተናገሩት፡፡
የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባዔ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በመሪዎች ደረጃ የሚካሄደው ዋናው ጉባዔ ደግሞ የፊታችን እሁድ ይጀመራል፡፡
ምክር ቤቱ በመሪዎቹ ጉባዔ ለውሳኔ ሊቀርቡ የሚችሉ ሰነዶችንና ሌሎችንም አስፈላጊ ግብዓቶች ያዘጋጃል፡፡ በተጨማሪም በመሪዎቹ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ሆነው ሊነሱ በሚችሉ የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ህብረቱ በተያዘው ዓመት (እ.ኤ.አ 2020) ለማሳካት ያቀዳቸው ግጭትና ጦርነትን የማስቀረት እና የልማት መደላድሎችን የማመቻቸት ስራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በመገምገም አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል፡፡
የአህጉሪቱን የመልማትና የማደግ ፍላጎት ቀጣይነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ የበጀት፣የአጀንዳ 2063፣ የአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ፣አፍሪካ ባላት ዓለም አቀፋዊ ውክልና፣በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና በአህጉሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂም ላይ በስፋት ተወያይቶ የደረሰባቸውን የውሳኔ ሃሳቦች አዘጋጅቶ ለዋናው ጉባዔ ያቀርባል፡፡
በጉባዔው ከስርዓተ ጾታ እና እኩልነት፣ከኃይል ልማት ከሌሎች ጉዳዮችም ጋር በተገናኘ የሚካሄዱ የጎንዮሽ ውይይቶች ይኖራሉ፡፡