አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ም/ቤት 2 ቋሚና 5 ተለዋጭ መቀመጫ ያስፈልጋታል- ጠ/ሚ ዐቢይ
በተመድ 70 ዓመት ታሪክ አፍሪካ አሁንም እንደ ጀማሪ አጋር ነው የምትታየው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒሰስትሩ
የአፍሪካ በሚዲያው ዘርፍም የራሷን እውነት የምታንጸባርቅበት ሚዲያ ሊኖራት ይገባል
በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቢያንስ 2 ቋሚና 5 ተለዋጭ መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
35ኛዉ የመሪዎች ጉባኤ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉባኤው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአፍሪካ ህዝብ ድምጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽ እና ከፍ ብሎ ሊሰማ ይገባል ብለዋል።
“አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ70 ዓመት በላይ ውክልና አላት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አፍሪካ አሁንም እንደ ጀማሪ አጋር መታየት የለባትም” ብለዋል
“የተመድ አሰራር ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ትክክለኛው ሰዓት ነው፤ ሁሉም በእኩል የሚስተናገዱበት መድረክ ሊፈጠር ይገባል” ሲሉም ጠይቀዋል
“አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቢያነስ 2 ቋሚ መቀመጫ እና 5 ተለዋጭ መቀመጫ ሊኖራት ይገባልም” ብለዋል።
የአፍሪካ በሚዲያው ዘርፍም የራሷን ድምጽ የምታሰማበት አህጉራዊ መገናኛ ብዙሃን ሊኖራት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢ አህመድ አስታውቀዋል።
“አሁን ያሉት መገናኛ ብዙሃን አፍሪካን በጦርነት፣ በረሃብ እና በሌሎች መጥፎ ገጽታዎች ሲያነሱ ነው የሚታየው፤ ይህንን ለማስቆምም መፍትሄው አፍሪካ የራሷ የሆነ ሚዲያ እንድታቋቁም ማድረግ ነው ብለዋል።
“ጉባዔው አፍሪካ የራሷ የሆነ የሚወክላት የአፍሪካን እውነታ ለዓለም የሚያንፀባርቅ ሚዲያ ለማቋቋ የሚያስችል ውሳኔ እንዲያሳለፍ እጠይቃለሁ” ብለዋል።
“ሰላምና ፀጥታ የአፍሪካ ሌላኛው ፈተና ነበረ፤ በሀገሬ ኢትዮጵያም ያጋጠመው ግጭት ሌላኛው ፈተና ነበር ሲሉም” አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር ህግን የማስከበር ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ “ችግሩን በራሳችን አቅም ለመፍታት የምናደርገው ጥረት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የበለጠ ተባብሶ ነበረ” ብለዋል።
“ምን እንኳ በዛ በኩል (ህወሓት) ግትርነት ቢኖርም የተናጠል ተኩስ በማቆም ከክልሉ ከመውጣት ውጭ ህግና ስርዓትን ለማስፈን የሚያስችሉ ሌሎች እርምጃዎችን ወስደናል” ብለዋል።
“ከዚህም ባሻገር ለሰላም መደላድልን ለመፍጠር በማሰብ ከፍተኛ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ጭምር ከእስር ለቀናል፤ በሃገራችን ሰላም እስኪመጣ ድረስ ሳንጥለው የሚቀር ጠጠር አይኖርም” ሲሉም ተናግረዋል በመክፈቻ ንግግራቸው፡፡
ለብሔራዊ ምክክር የሚሆኑ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳውቀዋል።
ለአፍሪካ እንደ ሌላ ፈተና ያነሱት ጉዳይ የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጋጥሙ የኢኮኖሚ መዋዠቆችን ለመቀንስ የጋራ የሆነ የአፍሪካ የንድግ ቀጠና መፍጠር ይገባልም ብለዋል።