1 ሺህ የማራቶን ውድድሮችን ያጠናቀቁት እንግሊዛዊ ክብረወሰን ሰበሩ
ለ43 አመታት ማራቶን የሮጡት የ61 አመቱ አዛውንት ውድድሩን ያጠናቀቁበት አማካይ ጊዜ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ እንዲሰፍሩ አድርጓቸዋል
51 ሰዎች 1 ሺህ ጊዜ የማራቶን ውድድርን በማጠናቀቅ ስማቸውን ማስመዝገብ ችለዋል
እንግሊዛዊው የ61 አመት አዛውንት 1 ሺኛ የማራቶን ውድድሮችን ከሰሞኑ አጠናቀው አዲስ ክብረወሰን አስመዝግበዋል።
ስቲቭ ኤድዋርድስ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድራቸውን ያጠናቀቁት በ18 አምታቸው ነበር።
ከዚያ ወዲህም ላለፉት 43 አመታት 1 ሺህ ጊዜ ከ42 ኪሎሜትር በላይ የሚረዝመውን ውድድር ማጠናቀቅ ችለዋል።
የመጨረሻ ውድድራቸውንም ባለፈው እሁድ በተካሄደው የሚልተን ኬይንስ ማራቶን አድርገዋል።
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብም ኤድዋርድስ አዲስ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገባውን አስታውቋል።
51 ሰዎች 1 ሺህ የማራቶን ውድድሮችን ማጠናቀቅ ቢችሉም ኤድዋርድስ ያስመዘገቡት አማካይ ፈጣን ስአት ክብረወሰን እንዲሰብሩ አድርጓቸዋል ይላል የዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል ዘገባ።
አዛውንቱ 1 ሺህ የማራቶን ውድድሮችን ለማጠናቀቅ 3 ሺህ 214 ስአት ፈጅቶባቸዋል። ይህም በአማካይ አንድ የማራቶን ውድድርን ለማጠናቀቅ 3 ስአት ከ21 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ ወስዶባቸዋል ማለት ነው።
አማካይ ውጤቱ በኬንያዊው ኬልቪን ኬፕቱም ከተያዘው የማራቶን ክብረወሰን (2 ስአት ከ35 ሰከንድ) አንጻር በ1 ስአት ከ21 ደቂቃዎች ቢዘገይም 1 ሺህ ማራቶኖችን ከሮጡት ፈጣን በመሆኑ ነው በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸው የሰፈረው።
1 ሺህ የማራቶን ውድድርን በማጠናቀቅ ስማቸውን ያስመዘገቡ ሯጮች ውድድሩን ያጠናቀቁበት በአማካይ ከአራት ስአት በላይ ነው።
ኤድዋርድስ ላለፉት 36 አመታት በአማካይ በየ13 ቀኑ ማራቶን ሮጠዋል።
ሩጫን በግራ እጃቸው ተፈጥሮ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን መገለል መርሻ አድርገው የጀመሩት እንግሊዛዊ፥ ስፖርት መከባበርና ፍቅር የሚገለጽበት መድረክ ነው ይላሉ።
1 ሺህኛ የማራቶን ሩጫቸው በውድድር ደረጃ የመጨረሻቸው ይሁን እንጂ “የአካል ብሎም አዕምሮ መድሃኒት” ነው የሚሉትን ሩጫ ግን እንደማያቆሙ ተናግረዋል።
“አቅማችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ሳትመለከቱ ህልማችሁን ተከተሉ” የሚሉት ስቲቭ ኤድዋርድስ፥ ሩጫን ለበጎ አላማም ተጠቅመውበት በባለቤታቸው ለሚተዳደር የበጎ አድራጎት ተቋም ከ10 ሺህ ፓውንድ በላይ ማሰባሰብ ችለዋል ተብሏል።