የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ ኢራን እና አጋሮቿ ለእስራኤል ጫና አይንበረከኩም አሉ
የሄዝቦላህ መሪ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለ በኋላ ተሸሽገው የቆዩት ካሚኒ ከሳምንት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በቴሌቪዥን ታይተዋል
እስራኤል በቀጠናው እያደረሰች ያለችው ጥቃት ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ አያደርገንም ያሉት መሪው ታሊባን ከኢራን እና አጋሮቿ ጋር አብሮ እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ ኢራን እና አጋሮቿ ለእስራኤል ጫና አይንበረከኩም ብለዋል።
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስረላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለ በኋላ ተሸሽገው የቆዩት የኢራኑ ሀይማታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ ከሳምንት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በቴሌቪዥን ታይተዋል፡፡
በዛሬው እለት በተሄራን የተካሄደውን የአርብ ጸሎት የመሩት ሀሚኒ እስራኤል በሊባኖስ እና በጋዛ እያደረስችው ለምትገኘው ጥቃት ኢራን እና ቀጠናዊ አጋሮቿ ወደ ኋላ አይሉም ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ በቴልአቪቭ 200 የሚደርሱ ባለስቲክ ሚሳይሎችን በማስወንጨፍ ለሀማስ እና ለሄዝቦላህ መሪ ግድያ የአጸፋ ምላሽ የሰጠችው ኢራን ከእስራኤል ሊሰነዘርባት ለሚችል ጥቃት በተጠንቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡
ካሚኒ በንግግራቸው “የማክሰኞው የተሄራን ጥቃት ህጋዊ እና ተገቢ ነው፤ የእስራኤልን ህገ ወጥ ድርጊት ለመቀልበስ የምናደርገው ትግል መሪዎች እየተገደሉም ቢሆን አይቋረጥም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጋዛ እየደረሰ የሚገኘውን ጭፍጨፋ እና በሊባኖስ የሚፈጸመውን ጥቃት በመቃወም የየመኑ ሁቲ እና በኢራቅ የሚገኙ ታጣቂዎች እንዲሁም ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተናግረው፣የአፍጋኒስታኑ ታሊባን ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሁለት አስርተ አመታት ጦርነት በኋላ አፍጋኒስታንን ማስተዳደር የጀመረው ታሊባን መንግስቱን ገና በማደላደል ላይ ሲሆን በምዕራባውያን እና በተባበሩት መንግስታት የተጣሉበትን ማዕቀቦች ለማስነሳት በድርድር ላይ ይገኛል፡፡
አስተዳደሩ ለኢራን ጥሪ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም ከሚገኝበት ሁኔታ አንጻር በዚህ ጦርነት ተሳትፎ ከምእራቡ አለም ጋር ያለውን ተቃርኖ የማስፋት ፍላጎት እንደማይኖረው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሀይማኖታዊ መሪው የሄዝቦላ ምትክ ይሆናሉ ተብለው ስለሚጠበቁት ሃሺም ሰይፈዲን በንግግራቸው ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም የሀሺም ወንድም እና በኢራን የሄዝቦላ ተወካይ ሰይድ አብደላ ሰይፈዲን በጸሎት ስነስርአቱ ላይ ከጎናቸው ተቀምጠው ታይተዋል፡፡
እስራኤል ምሽቱን በቤሩት በፈጸመችው ጥቃት የናስረላህ ተተኪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ሃሺም ሰይፈዲን ይገኙበታል የተባለ የመሬት ውስጥ ዋሻ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሟ አስታውቃለች፡፡
ሆኖም እስካሁን ከሄዝቦላህም ሆነ ከእስራኤል በናስረላህ ተተኪ ላይ ጉዳት ስለመድረሱ እና አለመድረሱ ማረጋገጫ የሚሰጡ መረጃዎች አልወጡም፡፡
በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው መግለጫ በትላንትናው እለት በቤሩት በፈጸምኩት የተጠና ጥቃት የሄዝቦላህ የኮምንኬሽን ሃላፊን ገድያለሁ ብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናዊ ግጭት ይከሰታል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የ21 ቀናት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡