የሱዳን ተፋላሚዎች እስካሁን ተኩስ ለማቆም አልተስማሙም፤ በካርቱም ጦርነቱ ቀጥሏል
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ዘረፋው መጨመሩን እና ከፍተኛ የአየር ድብደባ እየተፈጸመ መሆኑን ነዎሪዎች ተናግረዋል
ካርቱም በአየር ድብደባ እና ዝርፊያ እየታመሰች ነው ተባለ
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ዘረፋው መጨመሩን እና ከፍተኛ የአየር ድብደባ እየተፈጸመ መሆኑን ነዎሪዎች ተናግረዋል።
ሁለቱ ተፋላሚዎች ኃይሎቾ የአጭር ጊዜ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እየሰሩ መሆናቸውን አደራዳሪዋ ሳኡዲ አረቢያ ገልጻለች።
የሱዳን ጦሩ በትናንትናው ዕለት በካርቱም መሃል እና በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት አካባቢ ከፍተኛ የአየር ድብደባ መፈፀሙን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተቆጣጥረነዋል ያሉት ቤተ መንግስት በሱዳን ጦር የአየር ድብደባ ተመትቶ መውደሙን ገልጸዋል።
የሱዳን ጦር ግን ይህን ክስ አስተባብሏል።
ከተቀሰቀሰ ሶስተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እና ሰብአዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
በሱዳን ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በአንድ ሳምንት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ማደጉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታወቋል።
በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ማክበር ያልቻሉት ሁለቱ ሃይሎች ባለፈው ቅዳሜ እለት ተወካዮቻቸውን ወደ ሳዑዲ የወደብ ከተማ ጅዳ ልከው እየተነጋገሩ ነው።
የሳኡዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት እንዳስታወቀው ድርድሩ የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ ነው ሲሉ ተናግሯል።
ሱዳን በሰብአዊ ቀውስ አፋፍ ላይ ትገኛለች ያለው ተመድ ሁለቱ ኃይሎች የሰብአዊ እርዳት የሚያልፍበትን ኮሪደር በመክፈት ጉዳይ መስማማት አለባቸው ብለዋል።