ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለንግግር ሳዑዲ አረቢያ መግባታቸው ተነገረ
ሁለቱም ወገኖች የሱዳንን ህዝብ ጥቅምን በማገናዘብ ግጭቱን ለማስቆም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል
የሱዳን ጦር ውይይቱ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ያለመ ነው ብሏል
የሱዳን ኃይሎች በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ውይይት ዛሬ ሊያደርጉ መሆኑ ተነግሯል።
አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ በጋራ ባወጡት መግለጫ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል "የቅድመ ድርድር ንግግር" በጅዳ ሊጀመር መሆኑን በደስታ ተቀብለዋል።
ሆኖም አርብ ዕለት በካርቱም ግጭቱ ስለመቀጠሉ ተዘግቧል።
የሱዳን ጦር ውይይቱ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ያለመ ነው ብሏል። ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን ይፋዊ አስተያየት አልሰጠም።
ጦሩ ድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ወደ ጅዳ ልዑካን መላኩን ያረጋገጠ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ረድኤት ድርጅቶች በሱዳን ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ በማገጠሙ ለንግግር ጫና ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ከባድ ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተገድለዋል፤ ወደ 450 ሽህ የሚጠጉ ንጹሀን ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት እንዳው ከ115 ሽህ በላይ የሚሆኑት ሱዳናዊያን በጎረቤት ሀገራት ተጠልለው ይገኛሉ።
የሱዳኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጋር መራራ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ናቸው።
የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ መንግስታት መግለጫ "ሁለቱም ወገኖች የሱዳንን ህዝብ እና ጥቅም በማገናዘብ የተኩስ አቁም እና ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ውይይት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እናሳስባለን። ይህም የሱዳንን ህዝብ ስቃይና መከራ የሚታደግና ለተጎዱ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስን የሚያረጋግጥ ነው" ብለዋል።
የጋራ መግለጫው ሁሉንም የሱዳን ወገኖች ለሚያካትት የድርድር ሂደት በር እንደሚከፍት ተስፋውን ገልጿል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።