በሱዳን የተኩስ አቁም ቢታወጅም በማዕከላዊ ካርቱም ከባድ ውጊያ ሲደረግ መዋሉ ተገለጸ
የሱዳን ጦር እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ዛሬ 20ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ሁለቱ ኃሎች ትናንት ለ7 ቀን የሚቆይ የተኩስ አቁም ቢያውጁም በማዕከላዊ ካርቱም ከባድ ውጊያ እየተደረገ መዋሉን ነው የአይን እማኞች ያስታወቁት።
የሱዳን ጦር በፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግስት እና በጦር ኃይሉ ዋና መስሪያ ቤት ዙሪያ የሚገኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ለመግፋት እየተፋለመ ነው ተብሏል።
ይህም በሱዳን ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስን የማይቻል አስመስሏል።
ከሁለት ሳምንታት በላይ በዘለቀው ጦርነት የሁለቱም አንጃ መሪዎች ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ቢያሳዩም፤ ኃይሎቹ ከማንኛውም ድርድር አስቀድሞ ዋና ከተማዋን ካርቱምን ለመቆጣጠር እየታገሉ ነው ተብሏል።
በኦምዱርማን እና ባህሪ አጎራባች ከተሞች ላይ ከባድ የቦምብ ድብደባም ስለመፈጸሙ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሁለቱም ወገኖች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደርሱም፤ ጥሰውታል። የካርቱም ነዋሪዎች "ከትናንት ምሽት ጀምሮ እንዲሁም ዛሬ ማለዳ የአየር ድብደባዎች እና የተኩስ ድምጾች አሉ" ብለዋል።
ሚያዝያ 15 በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ሌሎች ሀገራት ሊተርፍ የሚችል ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
ሱዳን ባለፈው ማክሰኞ እንዳስታወቀችው በግጭቱ እስካሁን 550 ሰዎች ሲሞቱ 5 ሽህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ወደ 100 ሽህ የሚጠጉ ሰዎች ምግብና ውሃ በመገደቡ ከሱዳን ተሰደው ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ተመድ ገልጿል።