በኢትዮጵያ 4 ሺህ 800 የኩላሊት እጥበት እያደረጉ ከሞት ጋር የሚታገሉ ህሙማን መኖራቸው ተገለጸ
የኩላሊት እጥበት አገልግሎትን በ5 እጥፍ ያሳድጋል የተባለ ማዕከል በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ተመረቀ
አሁን ባለው ሁኔታ ታማሚዎች ለአንድ የኩላት እጥበት በአማካይ እስከ 3 ሺህ ብር ይከፍላሉ
በኢትዮጵያ ከ4 ሺህ በላይ የኩላሊት እጥበት (ዲያላሊስ) እያደረጉ ከሞት ጋር የሚታገሉ ህሙማን መኖራቸው የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ገለጸ።
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን አሰፋ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኩላሊት ህመም የሁሉም ሰው ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል ብለዋል።
አቶ ሰለሞን አከልውም፤ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የኩላሊ4 ሺህ 800 የኩላሊት እጥበት (ዲያላሲስ) እያደረጉ የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።
የኩላሊት ህመም ኖረዋቸው የዲያላሲስ አግልገሎት የሚያገኙ እንዳሉ ሁሉ ፤ዲያሊስስ ማድረግ አቅቷቸው “ኩላሊታችሁ ስራ አቁሟል” ሲባሉ ወደ ጸበል እና ወደ ተለያዩ አማራጮች የሚሄዱ በጣም በርካታ መሆናቸውም ተናረዋል።
አቶ ሰሎሞን፤ የኩላሊት ህሙማንን ሲቃይ ለማቃለል በመንግስት እየተሰሩ ያሉ የማስፋፍያ ስራዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።
“እንደ ድርጅት ችግሩን ለማቃለል የማስፋፋት ስራ እንዲከናወንና ንቅለ ተከላ እንዲጀመር የጤና ሚኒስቴርን ስንጠይቅ ነበር” ያሉት አቶ ሰሎሞን ፤ “መንግስት ምላሽ መስጠት መጀመሩ የሚመሰገን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በዛሬው እለት “በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ተገንብቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመረቀው የኩላሊት እጥበት ማዕከል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠቱን የሚያመላክት ነው” ሲሉም አክለዋል።
አዲሱ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ፤ ቀድሞ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአምስት እጥፍ የሚያሳድግ ነው መሆኑ ተነግሮለታል።
ዛሬ ወደ ሚኒልክ ሆስፒታል የገቡት 30 ማሽኖች መሆናቸውን የገለጹት የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪጁ፤ አንዱ ማሽን ሁለት የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) የሚያስፈልጋቸውን የኩላሊት ህሙማን የማጠብ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
አቶ ሰሎሞን “ይህ ማለት 30 ማሽኖች ጠዋት እና ማታ እየሰሩ በቀን እያንዳንዳቸው 60 ሰዎች በጠቅላላ ለ120 ሰዎች የእጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል” ብለዋል።
አዲሱ ማሽን በአንድ ጊዜ ሶስት ታማሚዎች እንኳን ማጠብ ቢጀምር በቀን 180 ሰው እጥበት ሊያገኝ እንደሚችልም አስታውቀዋል።
ይህ ከተደረገ የድሀ ድሃ ተብለው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ታማሚዎች በተዘጋጁ መስፈርቶች መሰረት በዘውዲቱ ሆስፒታል አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረግ እንደነበር ሁሉ፤ በምኒሊክ ሆስፒታል ተመሳሳይ አግልገሎት እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን።
“በተጠባባቂ ዝርዝር ውስጥ ያሉ 120 የሚሆኑ ህሙማኖች ከግል ክሊኒኮች ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል መጥተው አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ይኖራል ብለን እየጠበቅን ነው” ብለዋል።
የኩላሊት እጥበት ማዕከላት ማስፋፋት ቢያንስ ውጭ በግል የህክምና ማዕከላት ላይ ያለው የዋጋ ንረት የሚያረጋጋ ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን፤ አሁን ባለው ሁኔታ ታማሚዎች ለአንድ እጥበት በአማካይ የሚከፍሉትን 3 ሺህ ብር እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።
የኩላሊት ታማሚዎች ችግር ለማቃለል፤ የዲያሊሲስ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች ነጻ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር አልያም 500 ብር ከፍለው በዝቅተኛ ዋጋ የእጥበት አግልግሎት የሚያገኙበት እድል መንግስት ያመቻቻል የሚል ተስፋ እንዳለቸውም አቶ ሰሎሞን ገልጿል።
“አሁን ባለው መረጃ 4 ሺህ 800 የኩላሊት እጥበት (ዲያላሲስ) እያደረጉ ከሞት ጋር የሚታገሉ ህሙማን አሉ” ያሉት አቶ ሰሎሞን፤ የታማሚዎች ህይወት ለማቆየት ቀን ከሌት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
አቶ ሰሎሞን፤ መንግስት 1 ሺ 410 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶናል በዚህም በቦታው የኩላሊት ንቅለ ተከላን ጨምሮ ተለያዩ አግልግሎቶች የሚሰጡበት ሁለ-ገብ ማእከል እንገነባለንም ብለዋል።
ማዕከሉ ግንባታው ካለቀ በኋላ ከኪራይ ከሚገኘው ገቢ በክፍለ ሀገር ያሉ የኩላሊት ታማሚዎች ለመደገፍ እንደሚሰራም አስታውቋል።