ከኮሮና ህመም ያገገመ ሰው ምን ዓይነት ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ሊገጥሙት ይችላሉ?
ሆኖም የተጓዳኝ ችግሮቹ ደረጃና የጉዳት መጠንን በተመለከተ በውል የታወቀ ነገር የለም
የሳንባ ቁስለት፣ የኩላሊት፣ የልብ እና የጭንቅላት ጤና እክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጥናቶች አሳይተዋል
ከኮሮና ህመም ያገገመ ሰው ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ሊገጥሙት ይችላሉ?
የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) በአለማችን ከተከስተ ዕለት አንስቶ እስካሁኑ ደቂቃ ድረስ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህመም አጋልጧል፤ የበርካታ ሰዎችን ህይወት ነጥቋል ከፍተኛ ማህበራዊ ስነ-ልቦናዊ እና ምጣኔሃብታዊ ቀውሶችንም አስከትሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከተከሰተበት እና የመጀመሪያው የቫይረሱ ታማሚ ከተገኘበት ከወርሃ መጋቢት ጀምሮም 48 ሺ 140 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 17 ሺ 415 ሰዎች አገግመዋል 357 ሰዎች በፅኑ ታመዋል የ750 ህሙማን ህይወትም አልፏል፡፡
ወረርሽኙ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በሽታውን የተመለከቱ እውነታዎች ገና በመጠናት ላይ ናቸው፡፡ ገና ያልተደረሰባቸው ዘርፈ ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡ ክትባቶቹን ጨምሮ በቫይረሱ ተይዘው በሚያገግሙ ሰዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለው የጎንዮሽ ችግርም ገና በመጠናት ላይ ናቸው፡፡
ከህመሙ ያገገመ ሰው ምን አይነት ተጓዳኝ የጤና እክሎች ሊገጥሙት ይችላሉ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናቶች በመደረግ ላይ ናቸው የሚለው የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሳንባ ቁስለት፣ የኩላሊት፣ የልብ እና የጭንቅላት ጤና እክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጥናቶች አሳይተዋል ይላል፡፡
የሳንባ ቁስለቱ በህመሙ ጊዜ በአይን የማይታዩ ለኦክስጅን ዝውውር የሚረዱ የሳንባ ክፍሎች ላይ በሚፈጥረው ችግር ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ ችግሩ የሚያጋጥማቸው ሰዎች በተከታታይ እንደትንፋሽ ማጠር፣ ደረቅ ሳል የመተንፈስ ችግር ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን በእድሜያቸው ትንሽ የሆኑ ወጣት እና ጎልማሳዎች ከበሽታው ሊያገግሙ ቢችሉም በቻይና፣ ቪየና እንዲሁም በቅርብ በ20 ዓመት የቺካጎ ነዋሪ ላይ የተደረገው የሳንባ ንቅለ ተከላ በሽታው የሚያመጣው የሳንባ ቁስለት የጎላ ተጵፅኖ እንዳለው አሳይተዋል ይላል የተቋሙ መረጃ፡፡
ሌላው በረጅም የጤና እክል የሚጎዳው አካላችን የአንጎል እና የነርቭ ስርአት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ካገገሙ በኋላ እንደራስ ምታት፣ መፍዘዝ፣ ነገሮችን በትኩረት አለማሰብ ወይም የማስታወስ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡
ተመራማሪዎቸ ይህ የጤና ችግር ሊከሰት የሚችለው በበሽታው ምክንያት አንጎል ላይ በኦክስጅን እጥረት በሚመጣው ጉዳት እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ቫይረሱ በልብ ጡንቻ ላይ ከሚኖረው ተጽእኖ ጋር ተያይዞ የልብ ህመም እና ድካም በብዙዎቹ ታማሚዎች ላይ እንደሚያደርስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
እነዚህ የልብ፣ የሳንባ እና የደም ቧንቧ ችግሮች በኮሮና ቫይረስ ቤተሰብ በሆነው በሳርስ ታማሚዎች ላይ በተደረገ ጥናት 44 በመቶው የሚሆኑት ላይ ቫይረሱ ከተያዙ ከ12 አመት በኃላ ቢከሰትም በኮቪድ-19 ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከሰቱ በሽታው ምን ያክል አስጊ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ ችግሮች ከፅኑ ህመም ባገገሙ ታማሚዎች ላይ ጎልተው ሊታዩ እንደሚችሉ ጥናቶች ቢያሳዩም ምን ያህሉ እንዲሁም የትኞቹ የማህበረሰብ ክፍሎች የጤና እክሉ እንደሚያጋጠሟቸው ለማወቅ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡
ስለሆነም ማህበረሰቡ ማገገም ማለት ወደሙሉ ጤነኝነት መመለስ ላይሆን እንደሚችል በመረዳት ቫይረሱን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን እና የእጅ ንፅህንና በመጠበቅ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በትክክል በመጠቀም ራሱንም ሌላውን ከወረርሽኙ ሊጠብቅ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡