ፕሬዝዳንት ፑቲንና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን የመኩሩባቸው አንኳር ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲንና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም የአሜሪካን ዛቻ ቸል በማለት ተገናኝተው መክረዋል
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን “ሩሲያ ጠላቶቿ ላይ ታላቅ ድል ትቀዳጃለች” ብለዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ልዩ በተባለ ጉባኤ ላይ ተገናኝተው መወያየታቸው ታውቋል።
መሪዎቹ በወታደራዊ ጉዳዮች፣ በዩክሬን ጦርነትና በፒዮንግያንግ ሚስጥራዊ የሳተላይት መርሀ-ግብር ላይ መምከራቸው ተዘግቧል።
ፑቲን በሩሲያ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘውን የተራቀቀ የጠፈር ምርምር ማዕከል ለኪም ያስጎበኙ ሲሆን፤ የሰሜን ኮሪያን ጠፈርተኞች ወደ ጠፈር በሚጓዙበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረዋል ነው የተባለው።
በውይይቱ ወቅትም ፕሬዝዳንት ፑቲን ለሰሜን ኮረያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን በሳተላይት ልማት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ቃለ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለሰሜን ኮሪያ ምን አይነት ሳተላይት እንደሚያቀርቡ በይፋ ባይገልጹም የስለላ ሳተላይት ሊሆን እንደሚችል ግን ተገምቷል።
በብረት ለበስ ባቡር ሩሲያ የገቡት የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በጉብኝታቸው ዘርዘር ያሉ ጥያቄዎች ጠይቀዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
መሪዎቹ ከሚንስትሮቻቸው ጋር ለበርካታ ሰዓታት በዘለቀው ንግግራቸው፤ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችንና የጋራ የትብብር መስኮች ላይ ተወያይተዋል።
ከውይይቱ በኋላ ኪም ለ"ታላቋ ሩሲያ"፣ ለኮሪያና ሩሲያ ወዳጅነት ጽዋ ያነሱ ሲሆን፤ ሩሲያ በጠላቶቿ ላይ ታላቅ ድል ታስመዘግባለች ሲሉም ኪም ተናግረዋል።
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የመሪዎቹ ንግግር ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አጋር ሀገራቱ በዋናነትም ኪም ለሩሲያ መሳሪያና ጥይት ሊያቀርቡ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።
ሀገራቱ በዩክሬን ጦርነት ፒዮንግያንግ ለሞስኮ መሳሪያ እያቀረበች ነው የሚል ክስ ሲነዝሩ ከርመዋል። ምንም እንኳ ስሜን ኮሪያና ሩሲያ ክሱን ውድቅ ቢያደርጉም።
በመሪዎቹ ንግግር ፑቲን ወታደራዊ ትብብር ላይ ስለመወያየታቸው የጠቆሙ ቢሆንም ጥቂት ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።