ፖለቲካ
ፑቲን የትራምፕ ክስ የአሜሪካ ፖለቲካ "መበስበሱን" ያሳያል አሉ
ፑቲን እንደገለጹት በትራሞፕ ላይ የሚካሄደው ሁሉ በአሜሪካውያን እና በመላው አለም ህዝብ ፊት እየቀረበ ያለ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ክስ ነው
ትራምፕ ስልጣን ላይ በቆዩባቸው አራት አመታት ከፑቲን ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ሲገልጹ ነበር
የሩሲያው ፕሬዝደንት ፑቲን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ክስ የአሜሪካ ፖለቲካ "መበስበሱን"ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።
ፑቲን በትራሞፕ ላይ የቀረቡት የወንጀል ክሶች የፖለቲካ በቀል እና የአሜሪካን መሰረታዊ የሆነ ሙስና የሚያሳዩ ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"የትራምፕን ክስ በሚመለከት፣ አሁን እየተካሄደ ያለው ጥሩ ነው። ምክንያቱም የአሜሪካ ፖለቲካ መበስበሱን እና ዲሞክራሲን ለሌሎች ማስተማር እንደማይችል ያሳየናል" ብለዋል ፑቲን።
ፑቲን እንደገለጹት በትራሞፕ ላይ የሚካሄደው ሁሉ በአሜሪካውያን እና በመላው አለም ህዝብ ፊት እየቀረበ ያለ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ክስ ነው።
የህዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ትራምፕ ለ2024 የሪፐብሊካን እጩ ሆነው የመቅረብ እድል አላቸው። ትራምፕ ስልጣን ላይ በቆዩባቸው አራት አመታት ከፑቲን ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ሲገልጹ ነበር። ነገርግን ተችዎች ትራምፕ ለፑቲን ተንበርካኪ ሆነዋል ሲሏቸው እንደነበር ይታወሳል።
ሩሲያ የምዕራባውያን አጋር ከሆነችው ዩክሬን ጋር ጦርነት መጀመሯን ተከትሎ የሩሲያ እና አሜሪካ ግንኙነት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቷል።