መሪዎቹ በውትድርና ትብብርና በመሳሪያ አቅርቦት ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሩሲያ በ'ልዩ ባቡር' ተሳፍረው ጉዞ መጀመራቸው ተነግሯል።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኻን በስም ያልጠቀሷቸውን የመንግስት ባለስልጣን መሰረት አድርገው ኪም ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ጉባኤ ለመቀመጥ ከፒዮንግያንግ መነሳታቸውን ዘግበዋል።
ኢንተርፋክስ የተባለ የሩሲያ መገናኛ ብዙኸንም ወደ ውጭ ሀገር እምብዛም የማይጓዙት ኪም በመጪዎቹ ቀናት የሩሲያን መሬት ይረግጣሉ ሲል ዘግቧል።
ክሬምሊን ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝዳንት ፑቲን በ'ምስራቅ የኢኮኖሚ ፎረም' ለመሳተፍ ቫልዲቮስኮፍ ወደ ተባለች ከተማ እንደሚያቀኑ አስታውቋል።
ሆኖም ከኪም ጋር ስለሚደረግ ውይይት ግን ያለው ነገር የለም።
ሰሜን ኮሪያ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሞስኮን ፊት ለፊት እየደገፉ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ባለፈው ሳምንት ፑቲን ከፒዮንግያንግ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ አጋርነት በሁሉም ዘርፍ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል።
የኪም የመጨረሻ የውጭ ሀገር ጉዞ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ሲሆን፤ በመጀመሪያቸው የምስራቅ ኢኮኖሚ ፎረም ለመሳተፍ ወደ ቫልዲቮስኮፍ አቅንተዋል።
ይህም ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የጀመሩት የኒውክሌር መሳሪያ ድርድር መክሸፉን ተከትሎ ነው።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኸን እንደዘገቡት ከሆነ ኪም እሁድ ዕለት ጉዟቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ ማክሰኞ ጠዋት ፑቲንን ያገኟቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ መሪዎች ንግግር በውትድርና ትብብርና በመሳሪያ አቅርቦት ስምምነት ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ተገምቷል።