የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
ኪም ከፑቲን ጋር ከመገናኘታቸው ከስአታት በፊት ፒዮንግያንግ ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች
ባለፉት አራት ወራት ሁለት ጊዜ ሳተላይት ለማምጠቅ ሞክራ የከሸፈባት ሰሜን ኮሪያ ከሞስኮ ድጋፍ እንደምታገኝ ይጠበቃል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ ምስራቃዊ ክፍል ተገናኝተዋል።
ፑቲን በሩሲያ አሙር ክልል ቮስቶችኒ ከተማ በሚገኘው ዘመናዊ የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ኪምን ሲቀበሏቸው “ስላየሁህ ደስ ብሎኛል” ብለዋቸል።
መሪዎቹ በአስተርጓሚዎች ሰላምታ ሲለዋወጡም የተደመጠ ሲሆን፥ የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከሉን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
ኪም ጆንግ ኡን ለተደረገላቸው የጉብኝት ግብዣና ደማቅ አቀባበል ፕሬዝዳንት ፑቲንን አመስግነዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከልኡካናቸው ጋር በሚያደርጉት ምክክር የጦር መሳሪያ ጉዳይ ይነሳል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ ፑቲን “በሁሉም ጉዳይ እንነጋገራለን” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በሩሲያ የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል የተካሄደውን ምክክር በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
18 ወራት ባለፈው የዩክሬን ጦርነት የጦር መሳሪያ ክምችቷ የቀነሰው ሞስኮ ከፒዮንግያንግ ድጋፍ እንዳታገኝም የማዕቀብ ማስጠንቀቂያቸውን ቀጥለዋል።
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ትብብራቸው ባለፈ በሳተላይት ቴክኖሎጂም በጋራ ለመስራት ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል እንደ ሬውተርስ ዘገባ።
የስለላ ሳተላይቶችን ለማምጠቀ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ኪም ጆንግ ኡን በአራት ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል።
ኪም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሩሲያን ዘመናዊ የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ሲጎበኙም በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውና የድጋፍ ቃል እንደተገባላቸው የሩሲያው ዜና ወኪል አርአይኤ ዘግቧል።
ፑቲን እና ኪም በዚሁ ማዕከል ውስጥ ባደረጉት ምክክር የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ እና የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ መሳተፋቸው ተገልጿል።
ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫም ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ ከምዕራባውያን ጋር የምታደርገው ጦርነት "የተቀደሰ" ነው ብለውታል፤ ሀገራቸው ለሞስኮ ድጋፏን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በሌላ ዜና ፑቲን እና ኪም ከመገናኘታቸው ከስአታት በፊት ሰሜን ኮሪያ ሁለት የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ከሀገር ወጥተው ፒዮንግያንግ ሚሳኤል ስታስወነጭፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
ኪም ጆንግ ኡን በ12 አመታት የስልጣን ዘመናቸው ከሀገራቸው የወጡት ሰባት ጊዜ ብቻ መሆኑንም የሬውተርስ ዘገባ ያሳያል።